Search

ባለግርማው የኢትዮጵያ ክንድ፦ የመጋቢት ፍሬ!

ሓሙስ መጋቢት 24, 2018 182

ጠንካራ እና ዘላቂ ሀገረ መንግሥት ሊገነባ የሚችለው ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከግለሰቦች ተጽዕኖ በፀዱ፣ ገለልተኛ እና ሕዝባዊ በሆኑ ጠንካራ ተቋማት ትከሻ ላይ ነው።

በተለይም የአንድን ሀገር ኅልውና፣ ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደኅንነት የሚያስጠብቁት የመከላከያ፣ የፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማት የሚገነቡበት የፍልስፍና መሠረት የትውልዱን እና የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ቁልፍ ምሰሶ ነው።

ይሁንና ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ይህንን መርሕ በተግባር ለማየት እና ዘላቂነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ረጅም እና ፈታኝ መንገድ መጓዝ ግድ ብሏት ቆይቷል።

የኢትዮጵያን የቅርብ ዘመናት የፖለቲካ ታሪክ ስንቃኝ፣ የሀገረ መንግሥቱን ቅቡልነት እና ቀጣይነት እንዲያረጋግጡ የሚጠበቁ ቁልፍ ተቋማት ራሳቸውን የቻሉ እና ገለልተኛ ሆነው ከመገንባት ይልቅ፤ የአንድ ቡድን ርዕዮተ ዓለማዊ ትርክት ዘብ፣ ሥርዓት ሳይሆን ቡድናዊ ተምኔት ጠባቂ እና ገለልተኝነት የሌላቸው ነበሩ። የየሥርዓቱ ፖለቲካዊ አየር በተለዋወጠ ቁጥር ተቋማቱም አብረው የሚቀያየሩ መሆናቸው ሀገራዊ መረጋጋትን ሲፈታተን ቆይቷል።

ተቋማቱ ለሕዝብና ለሀገር ሊኖራቸው የሚገባው ታማኝነት፣ ለፖለቲካ ፓርቲና ለቡድን ፍላጎት ከሚሰጡት ታማኝነት በማነሱ የተቋማት ብሔራዊ ባሕሪ ጠፍቶ ቆይቷል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት በልዩ ትኩረት ከወሰዳቸው ታሪካዊ እርምጃዎች ቀዳሚው፣ ይህንን የተቋማት ድቀትና ስብራት መጠገን እና መዋቅራዊ ሪፎርም ማድረግ ነው። በደኅንነት፣ በፖሊስና የመከላከያ ተቋማት ላይ የተደረገው ማሻሻያ ዋነኛ ትኩረት ተቋማቱን ከፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ጠባቂነት አላቆ፣ የኢትዮጵያ እና የዜጎቿ የጋራ ክብርና ደኅንነት ዘብ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

ይህ መሠረታዊ የዕይታ እና የአደረጃጀት ለውጥ፣ ተቋማቱ ለፖለቲካ ቡድኖች ታማኝ ከመሆን ወጥተው የሕዝብና የሀገር አገልጋይ ወደሚሆኑበት ምዕራፍ ያሸጋገረ ትልቅ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ስኬት ነው። 

የመጋቢቱ ለውጥ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት በገለልተኝነትና በሙያዊነት ላይ ተመሥርተው የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ፣ ራስ አስቀጥል እና ሀገር አስቀጣይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆን የተቋማቱ ኅልውና መሠረት እንዲሆን የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶች ተዘርግተዋል። ይህ የተቋማት ሪፎርም ከፖለቲካዊ ነፃነት ባለፈ፣ ሙያዊ አቅምን በማሳደግ ላይ አተኩሯል። የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን ለማዘመን በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ መዋቅራዊና ቴክኖሎጂያዊ ብቃት እንዲገነባ ተደርጓል።

ተቋማቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ ዘመኑ የደረሰበትን ዘመናዊ ትጥቅ በመታጠቅ፣ መረጃን መሠረት ባደረገ ትንተና በመመራት እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ የኢትዮጵያን አቅም እያሳደጉ ይገኛሉ።

የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሪፎርሙ የፈጠረው ነፃነት፣ ኢትዮጵያን ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ ሥጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል የሚችሉበት ቁመና ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል።

የዚህ ሪፎርም ውጤት በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የቀረ ሳይሆን፣ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በገጠሟት ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ በመስዋዕትነት ተለክቶ በተግባር የተፈተነ ሀቅ ነው።

ተቋማቱ ሀገራዊ ታማኝነታቸውን ጠብቀው፣ ከተልዕኳቸው ሳይዛነፉ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በተጨባጭ ማስጠበቅ መቻላቸው የሪፎርሙን ትክክለኛነት እና የሀገረ መንግሥት ግንባታው በትክክለኛ መሠረት ላይ መቆሙን ያረጋግጣል።

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፓርቲ ጋሻ ጃግሬነት ተላቀው ወደ ሀገር ዘብነት የተሸጋገሩበት ሪፎርም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሉዓላዊነት የሚያረጋገጥ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ተቋማቱ የፖለቲካ መሣሪያ መሆናቸው አብቅቶ፣ ገለልተኛ የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸው የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ትልቅ ትሩፋት ነው።

ሕዝብንና ሀገርን ብቻ የሚያገለግሉ ሙያዊ ብቃትን የተላበሱ እነዚህ ብሔራዊ ተቋማት፣ ኢትዮጵያን ለትውልድ የምትሻገር ጠንካራ፣ የጸናች እና አኩሪ ሀገር እንድትሆን በቀጣይም የላቀ ድርሻቸውን ይወጣሉ።

የኢትዮጵያውያን ደኅንነት እና የሀገር ሉዓላዊነት በማይናወጥ ጽኑ ተቋማዊ መሠረት ላይ ቆሟል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ