የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እውቅና እና ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም በዘርፉ ስልጠና መስጠት እንደማይችል አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ከኤፍኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ስልጠና የመስጠት መብት ያለው ራሱ ኢንስቲትዩቱ እና ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ተቋማት ብቻ ናቸው።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ስልጠናው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መሰጠት እንደሚጀምርም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ እስካሁን ድረስ ለማንኛውም ግለሰብም ሆነ ተቋም የማሰልጠንና የማስተማር ፈቃድ እንዳልሰጠ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ ይህንን መመሪያ ጥሶ ስልጠና ሲሰጥ የተገኘ አካል ሕጋዊ ቅጣት እንደሚጠብቀው አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም ራሱን ከአደናጋሪ ግለሰቦች እንዲጠብቅና አላስፈላጊ ለሆኑ ወጪዎች እንዳይዳረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በአዋጅ ቁጥር 510/2014 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በዘርፉ ከዓለም ጋር የተጣጣመ ማኅበረሰብን የማስተማር፣ የማሰልጠን እና ምቹ ምሕዳር የመፍጠር ተልዕኮ የኢንስቲትዩቱ መሆኑ ተገልጿል።
ስለሆነም ማንኛውም ዜጋ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመቀናጀት ማከናወን እንዳለበት ተመላክቷል።
የኢትዮጵያን የኤአይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይረዱ እንዲሁም ተቋማዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው በግለሰቦች የሚደረጉ የማሰልጠን ሙከራዎች ከእውቅና ውጪ መሆናቸውና ተጠያቂነት እንደሚያስከትሉ ተጠቁሟል።
በኃይለሚካኤል አበበ