Search

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ እና የካፒታል ገበያ ለውጦች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እየከፈቱ ነው - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 58

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ፣ በመሠረተ ልማት እና በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፎች የጀመረቻቸው ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ሰፊ ዕድል ይዘው መቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (/) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በለንደን በተካሄደው የዩኬ-ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ እንደገለጹት፣ ከእነዚህ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች መካከል ግንባታው የተጀመረው እና 12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት አንዱ ነው።

ይህም በአቪዬሽን፣ በኮንስትራክሽን፣ በቱሪዝም እና በሙያዊ አገልግሎት ዘርፎች ትልቅ መነቃቃትን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ሽግግር ላይ ትልቅ ሚና ያለው እና ግንባታው በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኘው 4 ቢሊዮን ዶላሩ የዳንጎቴ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አቅም የሚያሳይ ተጠቃሽ ኢንቨስትመንት ሆኗል።

በአገልግሎት ዘርፉ የተመዘገቡ ለውጦች፡-

የፋይናንስ ገበያ - ... 2025 ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (ESX) እና የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት መደረጉ ለአማካሪ ድርጅቶች እና ለካፒታል ገበያ ተዋናዮች አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ዲጂታል ኢኮኖሚ - የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ገበያ መግባት እና ሚሊዮኖችን በዲጂታል ክህሎት ያሠለጠነው "5 ሚሊዮን ኮደሮች" (5 Million Coders) ኢኒሼቲቭ ዘርፉን እያሳደጉት ይገኛሉ።

ጤና ጥበቃ - የሆስፒታሎች፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ የፋርማሲዩቲካልስ እና የዲጂታል ጤና መፍትሔዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ዕድሎችን መፍጠሩን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ሀገራችን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ውስጥ ያላት ተሳትፎ እና በምሥራቅ አፍሪካ ያላት ስትራቴጂያዊ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ እነዚህን ዕድሎች ይበልጥ እንደሚያጎላቸውም ገልጸዋል።

በዮናስ በድሉ