የኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፍ እመርታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
በኢትዮጵያ እና እንግሊዝ መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማሳደግ የተዘጋጀው የኢትዮ-እንግሊዝ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026 በለንደን ከተማ ተካሂዷል።
ቢልለኔ ስዩም ከፎረሙ ጎን ለጎን በተካሄደው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ዲጂታላይዜሽን ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ ስኬታማ የቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓን አስረድተዋል።
የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚያስመዘግቡትን እመርታዊ ዕድገትም ዲጂታል ቴክኖሎጂ እያሳለጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አምስቱ የብዝኃ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰሶዎችም በዲጂታል መሠረተ ልማት ታግዞ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ዘርፍ የኢትዮጵያ ብዝኃ ኢኮኖሚ መሰሶ አካል መደረጉም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን ነው ያስረዱት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የዲጂታላይዜሽን ሂደት ዋና ስትራቴጂ ደረጃዎችን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር እንዳስቻለም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የበለፀጉ ሀገራት ያለፉበትን ልምድ እና ተሞክሮ በመውሰድ እና ከነባራዊ አውድ ጋር በማጣጣም በወሳኝ የሽግግር ሂደት ላይ እያለፈች መሆኗን ገልጸዋል።
የዲጂታል ዘርፍ እመርታም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገትን በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
በፓናል ውይይቱ አወያይ የነበሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዘመዴነህ ንጋቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአስደናቂ የዕድገት ምዕራፍ እያለፈች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህም በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ዘርፍ የተመዘገበው እመርታዊ ውጤትም ንግድ እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ የትራንስፎርሜሽን ምኅዳር መፍጠሩን አስገንዝበዋል።