Search

ቻይና በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈች

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 75

ቻይና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ለሚመራውና በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ ለሆነው ብልፅግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ይፋ ባደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሠረት፥ ገዥው የብልፅግና ፓርቲ ከተወካዮች ምክር ቤት 501 መቀመጫዎች መካከል 438ቱን በማሸነፍ በድጋሚ መመረጡ ይታወቃል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉኦ ጂያኩን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ኢትዮጵያ የቻይና ስትራቴጂያዊ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ከራሷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስማማ የልማት ጎዳና እንድትከተል ቻይና ትደግፋለች ብለዋል።

ቃል አቀባዩ፥ ኢትዮጵያ በአመርቂ የልማት ጎዳና ላይ መሆኗን ገልጸው፤ ወደፊትም የላቀ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ቻይና ታምናለች ብለዋል።

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጠውና የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ስምምነቶች እንዲሁም በቤጂንግ የተካሄደውን የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) ውሳኔዎች ለመተግበር ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ይህም በተግባራዊ ትብብር የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ፣ እንዲሁም በቻይና-አፍሪካ እና ግሎባል ሳውዝ (አዳጊ ሀገራት) መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን ቃል አቀባዩ አክለው ገልጸዋል።