Search

የኢፌዴሪ መከላከያ አመራሮች ከጅቡቲ የፈረንሳይ ጦር አዛዥ ጋር በቀጣናዊ ደኅንነት እና ወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ተወያዩ

ሓሙስ ሰኔ 18, 2018 57

በጅቡቲ የፈረንሳይ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሴባስቲያን ቫሌት የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከኢፌዴሪ መከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በፀረ-ሽብርተኝነት፣ በጤና፣ በሥልጠና እና በቴክኒክ ድጋፍ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን በስፋት ተወያይቷል።

ልዑካን ቡድኑ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ባደረገው ቆይታ በቀጣናዊ ደኅንነት፣ በፀረ-ሽብርተኝነት እና በሁለትዮሽ የወታደራዊ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ መግባባት ላይ ደርሷል።

በውይይቱ ወቅት የፈረንሳይ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሴባስቲያን ቫሌት ኢትዮጵያ በአሸባሪው አልሸባብ ላይ እያካሄደች ያለውን ውጤታማ ዘመቻ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ ወዳጅነት እና ታሪካዊ ወታደራዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን የገለጹት አዛዡ፣ ይህንን ስትራቴጂካዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በአሸባሪው አልሸባብ ላይ ያስመዘገበችው አስደናቂ ወታደራዊ ድል በጠንካራ የሥነ-ልቦና ዝግጅት፣ በላቀ አካላዊ እና ታክቲካዊ ብቃት እንዲሁም በተቀናጀ የዘመቻ አፈጻጸም ላይ የተመሠረተ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄነራል ተሾመ ገመቹ በበኩላቸው፣ አሸባሪው አልሸባብ ላለፉት ሃያ ዓመታት የኢትዮጵያን ድንበር ለመሻገርና ጥቃት ለመሰንዘር በተደጋጋሚ የሞከረ ቢሆንም በአንድም አጋጣሚ ዓላማውን ማሳካት እንዳልቻለ አብራርተዋል።

ይህ ታላቅ አሀራዊ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው በጠንካራ የአመራር ብቃት፣ በተቀናጀ የሠራዊት ዝግጅት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በጥብቅ ዲስፕሊን እና በማይናወጥ የሕዝባዊ ድጋፍ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ የሁለቱ ወገኖች ውይይት የኢትዮጵያን እና የፈረንሳይን የቆየ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ከመሆኑም በላይ፣ የምሥራቅ አፍሪካን እና የዓለም አቀፉን የጸረ-ሽብር ትግል የሚያግዝ መሆኑ ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።