ኢትዮጵያ በያዘችው የለውጥ ጉዞ የጸጥታ መዋቅሯን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት እና ወታደራዊ ቁሶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለመገንባት የሚያስችል ታሪካዊ እርምጃ ወስዳለች።
ይህ አካሄድ ሀገራችን በወታደራዊ አቅም ረገድ የነበራትን የውጭ ጥገኝነት በመቀነስ የራሷን የጸጥታ ፍላጎት በራሷ አቅም የምትፈታበትን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ድሮን (UAV) ቴክኖሎጂን በሀገር ውስጥ የማልማት እና የመገጣጠም ሥራን በስፋት እየተገበረ ይገኛል።
የድሮን ማዕከላት መቋቋም እና በሥራ ላይ መዋል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአየር ክልሉን በአስተማማኝ ሁኔታ በመቆጣጠር እና የጸጥታ ስጋቶችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ አስችሎታል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ለቀላል እና ለከባድ የጦር መሣሪያዎች የሚያስፈልጉ ጥይቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመራቸው ሌላው ትልቅ ስኬት ነው።
ይህም በድንገተኛ የጸጥታ ተግዳሮቶች ጊዜ የጦር መሣሪያ እና ጥይት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም ዋስትና ከመስጠቱም በላይ፣ ለውጭ ግዥ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማዳን አግዟል።
ከዚያም አልፎ ሀገር ውስጥ የተመረተውን ጥይት ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ተጀምሯል።
ይህ በራስ አቅም ወታደራዊ ቁሶችን የማምረት ሂደት የኢትዮጵያን የመከላከል አቅም በማሳደግ የበኩሉን የላቀ ሚና አለው።
የጦር መሣሪያ ጥገና ማዕከላትን በማጠናከር እና ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ሠራዊቱ ለቴክኖሎጂው ጥገና እና ዝግጁነት ወደ ሌላ ሀገር መመልከትን አስወግዷል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂ እና የውኃ ላይ ደኅንነትን ታሳቢ ያደረገ የባሕር ኃይል ግንባታን ዳግም በማቋቋም እና በማጠናከር የተሟላ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት አራምዳለች።
የዚህ የራስ አቅም ግንባታ መሰረታዊ መልእክቱ ኢትዮጵያ ለሉዓላዊነቷ እና ለግዛቷ አንድነት የምትሰጠውን ቅድሚያ የሚያሳይ ነው።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ ወታደራዊ አቅም መገንባቷ ለተደቀኑባት ፈተናዎች እጅ እንደማትሰጥ እና የራሷን የጸጥታ አቅም በራሷ ዕውቀትና ሀብት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያረጋገጠችበት ማሳያ ነው።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የጦር መሣሪያ ማምረት እና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የኢትዮጵያን የጸጥታ መዋቅር ዘመናዊ ከማድረጉም በላይ ለረጅም ጊዜ የሰላም እና የልማት ጉዞ የጸና አቅም ሆኖ ቀጥሏል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት ከክላሽንኮቭ ጥይት ምርት ጀምሮ እስከ ድሮን ቴክኖሎጂ፣ የከባድ መሳሪያ ልማት እና የሳይበር ደህንነት አቅም ግንባታ ድረስ የተራዘመ ጉዞ አድርጋለች።
ይህ ለውጥ የመከላከያ ዘርፉን ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የኢንዱስትሪ ልማትን እና የሀገራዊ ሉዓላዊነት ግንባታን ጭምር የሚያሳይ ታላቅ እመርታ ነው።
በሃና ምንዳሁን