“ውይይት ማለት የራስን ሃሳብ በሌላው ላይ በሃይል መጫን ሳይሆን፣ የጋራ እውነትን ፍለጋ በአክብሮትና በክፍት ልቦና አብሮ መጓዝ ማለት ነው።”
ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ብቻ ሳትሆን፣ እጅግ የላቀና የዳበረ የውይይት፣ የሙግትና የአደባባይ ምክክር (Public Deliberation) ዕሴት የነበራት ታላቅ ሀገር ናት።
አባቶቻችን ከዘመናት በፊት ጀምሮ በየማህበረሰቡ ውስጥ በዛፍ ጥላ ሥር፣ በገዳ አደባባይ፣ በኦዳ ስር፣ በበላ ልበልሀ በመካቦንና በተለያዩ ባህላዊ ሸንጎዎች ተሰብስበው የህዝብን ጉዳይ በነጻነት ሲሞግቱና ሲመክሩ የኖሩ ናቸው።
በህዝቦች ዘንድ የአደባባይ ውይይቶች፣ ስነ-ምክንያታዊ ሙግቶች እና የተራቀቁ የሃሳብ ፍጭቶች ባህላዊ መገለጫችን ነበሩ።

ይሁንና፣ ይህ የዳበረና የሚያኮራ የውይይት ባህላችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደታችን ውስጥ ክፉኛ ተሰበረ።
የፖለቲካ ልሂቃኑ የሃሳብን ልዕልና ወደ ጎን በመተው፣ ወደ ጽንፍ የያዙ ትርክቶችና የዜሮ ድምር (Zero-sum) ፖለቲካ ውስጥ ገቡ።
በዚህም ምክንያት መወያየት እንደ ኃጢአት፣ መደማመጥ እንደ ሽንፈት፣ መቻቻልም እንደ ፍርሃት የታየበት ጨለማ ዘመን ውስጥ ወደቅን።
ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ፣ በመገዳደል፣ በጠመንጃ አፈሙዝና በደም ላይ የቆመ አግላይ ፖለቲካ ሲገነባ ቆየ።
ይህ በደም የታጠበ ፖለቲካ ሀገራችንን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈላት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታችንን እንዴት እንዳጨናገፈውና ህዝባችንን ለዘመናት በድህነትና በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዳቆየው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ይህንን አሳዛኝ የታሪክ አዙሪት በመቀየር፣ ኢትዮጵያን ወደ ታላቁ የውይይትና የምክክር ማዕድ የመለሳት የለውጡ መንግሥት መምጣት ነው።
የለውጡ መንግሥት የደም ፖለቲካን ምዕራፍ ዘግቶ፣ ሀገራችን ወዳዳበረችው ጥንታዊ የአደባባይ ውይይት (Public Deliberation) ባህል እንድትመለስ አዲስ በር ከፈተ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋምና ነፃ ሆኖ እንዲሰራ በማድረግ፣ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንድንፈታ መደላድሉን አመቻቸ።
ይህ መንግሥት ያመቻቸው ሀገራዊ ምክክር፣ ሀገራችን ከገባችበት ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስ የምትወጣበት የነፍስ አድን ገመድ ነው።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ተራ የፖለቲካ ክንዋኔ አይደለም። ይልቁንም የመዳኛ መንገዳችን ነው።
ላለፉት ዘመናት ተከማምረው የመጡ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ቁስሎቻችንን የምናክምበት፣ የቆሰለችው ኢትዮጵያ የምትፈወስበት ብቸኛ የህክምና ማዕከል ነው።
የሀገረ መንግሥት ማጽኛ ነው፤ በደም የተገነባውን የፖለቲካ ባህል አፍርሰን፣ በሃሳብ ላይ የተመሰረተ (Idea-based) ዴሞክራሲን የምንገነባበት ጠንካራ መሠረት ነው።
የአንድነት ድልድይ ነው፤ የብዝሃነታችን ውበት ተጠብቆ፣ የሁላችንም ድምፅ በእኩልነት የሚደመጥባትንና እያንዳንዱ ማህበረሰብ የባለቤትነት ስሜት የሚሰማባትን አዲስ ኢትዮጵያ የምንፈጥርበት ሂደት ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ለደረሰበት ወሳኝ ምዕራፍ ስኬት፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎና ጽናት ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ የምትድነው፣ የምትታከመውና የምትፈወሰው እኛው ራሳችን በክፍት ልቦና ስንወያይ ብቻ ነው።
በመሆኑም፣ መላው የፖለቲካ ኃይሎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ይህንን የለውጡ መንግሥት ያመቻቸውን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም ከምክክሩ ጎን በጽናት እንድትቆሙ ታሪካዊ ጥሪ ቀርቦላችኋል።
መገዳደልን፣ መነጠልንና የደም ፖለቲካን ታሪክ አድርገን፣ ወደ አባቶቻችን የውይይትና የሙግት አደባባይ እንመለስ። ልዩነቶቻችንን በጋራ ተባብረን ወደ ጥንካሬ እንቀይር።
ለዚህም ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በጽናትና በአንድነት ለሀገራችን ፈውስ በጋራ እንቁም!