ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን፣ በተለይም በዋና ከተማችን፣ እየታየ ያለው አስደማሚ የከተሜነት ትራንስፎርሜሽን እና ዘመናዊ የለውጥ ማዕበል የዘመናችን ትልቁ ማሳያ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ይህ የለውጥ እና የብልፅግና ጉዞ ግዑዝ በሆኑ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በማቅለል እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣትን ዋነኛ ግቡ አድርጎ እየተጋ ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረውን አድካሚ፣ ጊዜ አባካኝ፣ በቢሮክራሲ የተተበተበ እና ኋላቀር የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል፣ የለውጡ መንግስት ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን አሳይቷል።
የዚህ ታላቅ እና ሀገራዊ ራዕይ ዋነኛ አንጓ የሆነው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ዘመኑን የዋጀ አሰራር ለመዘርጋት እና ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረ የትውልድ ልቀት ፕሮጀክት ነው።
ይህ ስትራቴጂ ከተማዋ ዕለት በዕለት የምታስመዘግበውን ፈጣን ዕድገት እና «ስሉጥ ከተማ» (Smart-city) የመሆን ራዕይ በሚመጥን መልኩ፣ ቴክኖሎጂን ከነዋሪው የአኗኗር ዘይቤ ጋር እያዋሃደ ይገኛል።
የዚህ ስትራቴጂክ አቅጣጫ እና የዘመን ዝላይ ትልቁ ማሳያ ደግሞ «መሶብ» የተሰኘው አዲሱ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ነው።
መሶብ፣ በኢትዮጵያውያን የባህል እሴት የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አብሮነትን፣ እንግዳ ተቀባይነትን እና ማዕድን የሚያንፀባርቅ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ዛሬ ላይ ይህ ቃል አዲስ ትርጓሜ አግኝቶ የዘመናዊነት፣ የቅልጥፍና እና የስሉጥ አገልግሎት (Smart Service) ህያው ተምሳሌት ሆኗል።
ዕድገቷን እና ስሉጥ ከተማነቷን በሚመጥን ፈጣን አገልግሎት ለማቅረብ ቴክኖሎጂን ግብር ላይ የማዋል ሂደት ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ቀዳሚው እና ብሩህ ተጠቃሽ ሆኖ አደባባይ ወጥቷል።
መሶብ የዘመን ዝላይ የፈጠረው፣ የህብረተሰቡን የነገ ፍላጎት ዛሬ ላይ ቀድሞ ለመመለስ የተቃኘ የቴክኖሎጂ ትሩፋት ነው።
ይህን የአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የህብረተሰቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለማዘመን እና ለማሳለጥ ቀን ከሌሊት ያለእረፍት እየተሰራበት ይገኛል፤ በዚህም የላቀ እና አይን ገላጭ የሆነ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቦበታል፡፡
አገልግሎቱን ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ተደራሽ ለማድረግ፣ እስከአሁን ባለው ሂደት በማዕከል ደረጃ እና በዘጠኝ ክፍለ-ከተሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል።
ከዚህም ባለፈ፣ ቋሚ ማዕከላት ድረስ መምጣት ለማይችሉ ወይም አፋጣኝ አገልግሎት ለሚፈልጉ ነዋሪዎች፣ በተንቀሳቃሽ አውቶብስ (Mobile Bus) የተደራጀ፣ ፈጠራ የታከለበት እና ተደራሽነቱን ያሰፋ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
እነዚህ ማዕከላት የህዝብን አደራ ለመሸከም በሚያስችል መልኩ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግባቸው፣ ዘመናዊ አሰራርን የተላበሱ፣ እንዲሁም በስነ-ምግባር እና በዕውቀት ሙሉ በሙሉ የበቁ የሰው ሃይል የተሟላላቸው በመሆናቸው የአገልግሎት ጥራታቸው እጅግ የላቀ ነው።
ይህ የዘመን ዝላይ ያመጣው ስሉጥ አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ያሳደረው ተፅዕኖ እጅግ አዎንታዊ እና የሚያኮራ ነው።
በቅርቡ በቴክኖሎጂ በታገዘ እና ሳይንሳዊ መንገድን በተከተለ ዳሰሳ (Survey) እንደሚያሳየው፣ የአገልግሎቱ ተገልጋይ ከ99 በመቶ በላይ እርካታ (Customer Satisfaction) እንዳለው በግልፅ አረጋግጧል፡፡ ይህ አስገራሚ ቁጥር በወረቀት ላይ የሰፈረ አሃዝ ሳይሆን፣ የህብረተሰቡን ዳግም እምነት፣ የመንግስትን የለውጥ ፍሬ እና የትውልዱን የዲጂታል ልህቀት የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
በአጠቃላይ ፣ የመሶብ ዲጂታል አገልግሎት የ«ስሉጥ ከተማ» ራዕይ በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደበት ተግባራዊ ማሳያ ነው።
ትላንትናን በጉድለት እና በመሰልቸት ስናነሳው የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት፣ ዛሬ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አቅም ወደ የላቀ የእርካታ ደረጃ ማሸጋገር መቻላችን፣ እንደ ሀገር የጀመርነው የዘመን ዝላይ ትክክለኛ እና አስተማማኝ መንገድ ላይ መሆኑን በጉልህ ያረጋግጣል።
የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግቡን መምታት የጀመረው ገና ዛሬ በመሶብ አውድማ ላይ ነው። መሶብ ስሉጥ ከተማን በስሉጥ አገልግሎት እያጀበ፣ የትውልድ ልህቀትን በተግባር የሚያረጋግጥ የዘመናችን ብሩህ ፋና ወጊ ብርሃን ነው!