የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማው ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሥር በተቋም ግንባታና በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ በ10 ዙር ሲሰለጥኑ የነበሩ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮችን በዛሬው ዕለት አስመርቀዋል።


ከንቲባዋ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ኦፊሰሮቹ ከሕዝብ ጋር አክብሮት የተሞላበት ተግባቦት እንዲኖራቸው፣ ሕግና ሥርዓትን ያለ ምንም አድልዎ እንዲያስከብሩ እንዲሁም ፍጹም አገልጋይነትንና መልካም ሥነ-ምግባርን እንዲላበሱ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ተመራቂ ኦፊሰሮች ሕዝባቸውን በፍቅር፣ በትህትናና በማክበር እንዲያገለግሉ፣ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ የወጡ ደንቦችን ያለ ምንም ርኅራኄና አድልዎ የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የኦፊሰሮቹ ወታደራዊ አለባበስ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ እንዲሆን ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት ከነበረው በተጨማሪነት የሚያገለግል አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ተቋማት በሥርዓት የተገነቡ፣ ጠንካራ የአገልግሎት ሥርዓት ያላቸው፣ ሥነ-ምግባር የተላበሱና ለሕዝብ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎችንና አመራሮችን የመፍጠር ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
