ኢትዮጵያ በዓመት 33 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ማምረት መቻሏንና ይህም ቀደም ሲል በአፍሪካ ቀዳሚ የነበረችውን የግብፅን የ9.7 ሚሊዮን ቶን ምርት በሶስት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ዓመታት “በስንዴ ራሳችንን መቻል አለብን” ሲባል ጉዳዩ እንደ ቅዠት ይታይ እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ ግን በተግባር ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታን በምሳሌነት አንስተው፣ እያንዳንዱ ዶዘር እና ማሽነሪ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዘ የጥራት ቁጥጥር እያደረገ እንደሚሰራና ይህም የሰው ልጅ ሱፐርቪዥን ሳይፈልግ ጊዜና ገንዘብ እየቆጠበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በመከላከያ ዘርፍም ሀገራችን የድሮን ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባለፈ በስፋት ማምረት መጀመሯንና ወደ ውጭ በመሸጥ ላይ መሆኗን ይፋ አድርገዋል።
እነዚህ በስንዴ፣ በከተማ ኮሪደር ልማት፣ በኤአይ ዩኒቨርሲቲ እና በመሶብ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን በአፍሪካ የምርታማነትና የብልጽግና ተምሳሌት እያደረጓት መሆኑ ተገልጿል።