የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ወቅት ያሳየው ታማኝነት እና ፍቅር የመንግሥት አገልግሎት እንዲሻሻል እና ሌብነት እንዲቀንስ ባለው ፍላጎት በመሆኑ፣ ይህን አደራ መጠበቅ ካልተቻለ ቀጣይነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት አሁንም በየተቋማቱ በእጅ መንሻ እና በብልሹ አሰራር ምክንያት የሚማረሩ ዜጎች መኖራቸውን ተናግረው የኢትዮጵያ ህዝብ ስላከበረን አብዝተን ማክበር፣ ስላከበረን አብዝተን ማገልገል፣ ባከበረን ልክ ታምነን መገኘት አለብን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ዋነኛ ጥቅሙ ሰብዓዊ ንክኪን በመቀነስ ሌብነትን ማስቀረት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቢሮክራሲ መጉላላት ዜጎችን ለከፍተኛ ብስጭትና ለአደጋ እንደሚዳርግ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም እያንዳንዱ ተቋም ራሱን ፈትሾ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን በማሳደግ የህዝቡን የቅሬታ ምንጭ በአስቸኳይ ማድረቅ እንዳለበትና አሁን የተመዘገቡት ድሎች የህዝቡ ፍላጎት 1 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።