የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት ማብቃቱን ተከተሎ ታሪካዊው "የኢስላማባድ የመግባቢያ ስምምነት" በይፋ ተፈርሟል።

ይህ ስምምነት በፈረንሳይ ፓሪስ በሚገኘው የቨርሳይ ቤተ-መንግሥት በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በኢራኑ ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን መካከል በዲጂታል መንገድ የተፈረመ ሲሆን፣ በፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ አደራዳሪነትና በኳታር መንግሥት አጋዥነት የተደረሰ ነው።
በጠቅላላው 14 ነጥቦችን የያዘው ይህ ስምምነት ይፋ እንደተደረገም በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ1.12 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ ወደ 78.66 ዶላር ዝቅ ብሏል።
የስምምነቱ አንኳር ድንጋጌዎችም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሁሉም ግንባሮች፣ በተለይም በሊባኖስ በይፋ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት በአስቸኳይ እና በቋሚነት እንዲቆም የሚደነግግ ሲሆን፣ ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ወታደራዊ ጥቃት ላለመሰንዘር ቃል ገብተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለዓለም የነዳጅ ንግድ ወሳኝ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ ለ60 ቀናት ያህል ያለምንም ቀረጥ ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲሆን ተስማምተዋል።
በዚህም መሠረት በሚቀጥሉት 30 ቀናት ውስጥ ኢራን በሰርጡ ላይ የተተከሉ ፈንጂዎችን በሙሉ የምታጸዳ ሲሆን፣ አሜሪካ በበኩሏ የጣለችውን የባሕር ላይ እገዳ ሙሉ በሙሉ ታነሳለች።
ስምምነቱ እንደተፈረመ አሜሪካ በኢራን የነዳጅ ምርት ወጪ ላይ ጥላው የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳ የተደረገ ሲሆን፣ አሜሪካ ከቀጠናው አጋሮቿ ጋር በመተባበር በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባት ኢራን መልሶ መገንቢያ የሚውል ቢያንስ 300 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ለመመደብ ስምምነት ላይ ደርሳለች።

እንዲሁም ኢራን የኑክሌር መሣሪያ እንዳታመርት ወይም እንዳትገዛ የሚያግዱ ጥብቅ የቴክኒክ ድርድሮች በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ይህ የከፍተኛ መሪዎች ፊርማ ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ፊት የጸና ሕጋዊ ዋስትና እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ስምምነቱ ትልቅ ተስፋ ይዞ ቢመጣም፣ በእስራኤል በኩል በሁሉም የፖለቲካ መስመሮች ላይ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሕዝባቸው ቃል የገቡት የኢራንን መንግሥት የመጣልና የባሊስቲክ ሚሳኤል አቅሟን የማክሸፍ ዕቅድ በስምምነቱ ውስጥ ባለመካተቱ፣ እስራኤል በሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል የምታደርገውን የአየር ድብደባና የወታደራዊ ይዞታ የማስፋፋት ሥራ አሁንም ቀጥላበታለች።
በሌላ በኩል፣ የኢራን ዋና ተደራዳሪ መሐመድ ባገር ቃሊባፍ ኢራን ወደዚህ ድርድር የገባችው ከወታደራዊ ድል እና ከጠንካራ አቋም በመነሳት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም የኢራን የባሊስቲክ ሚሳኤል አቅም ፍጹም ለድርድር የማይቀርብ እና ለመተኮስ ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን በድጋሚ አስታውቀዋል።