በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ውስጥ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ጥራትና ፍጥነት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ቢሆንም፣ ለሀገር ዕድገት ተግዳሮት የሆኑት የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ብልሹ አሠራሮች እና ለዘመናት የቆየው የተበታተነ አሠራር ተገልጋዮች ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ እንዲንከራተቱ በማድረግ ጊዜና ጉልበታቸውን በከንቱ ሲያባክን ቆይቷል።
ኢትዮጵያም ይህንን በዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥር አሠራር ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ችግሮቹን ለመፍታት በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።

ይህንን ችግር ለመቅረፍና የመንግሥትን አገልግሎት ለዜጎች ቅርብ ለማድረግም፣ በተሟላ ማዕድ የሚወክለውን "መሶብ" በመግለጽ በአንድ ጣራ ሥር የተለያዩ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ አቀናጅቶ የሚሰጠው "መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት" እንደ ሀገር ብሎም በክልል ከተሞች ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተጀመረውና ክፍት የሆነ ይህ ማዕከል፣ መንግሥት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት ማረጋገጫና በኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ውስጥ እንደ ትልቅ የዕጥፋት ነጥብ የሚቆጠር ታላቅ ሥራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ ርምጃና የመንግሥት ቀልጣፋ፣ ተዓማኒና ቀጣይነት ያለው የሪፎርም ማሳያ የሆነው ይህ ማዕከል ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ በመሆኑ ዜጎች እጅግ የተሳለጠ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል።
የአሠራር ሥርዓቱ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን፣ ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን የሚያስቀር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ማዕከላቱ እየሰጡት ካለው ስሉጥ አገልግሎት ማረጋገጥ ይቻላል።
መሶብ አንድ ማዕከል የሕዝብን ፍላጎት ያማከለና ሁሉም ዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በአክብሮትና በኃላፊነት መንፈስ የሚገለገሉበት መሆኑ ዘመኑን የዋጀ የሚያደርገው ሲሆን፣ በተለይም ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ መስጠቱ ቀደም ሲል ይገጥማቸው የነበረውን እንግልት ለመቅረፍ አስችሏል።
በተጨማሪም አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ አሠራሩንና ጥራቱን ከማሻሻል ባለፈ ብልሹ አሠራርን በመከላከልና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ተጠቃሚዎች ያስረዳሉ።
ይህ ውጤታማነቱ በአዲስ አበባ የተረጋገጠውና ነዋሪዎች ሳይጉላሉ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ያለው "አዲስ መሶብ" ስኬታማ ተሞክሮ፣ ቴክኖሎጂን ከመሠረታዊ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት ከከተማ ወደ ክልል ከተሞች አስተዳደሮች በስፋት እየሰፋ በመሄዱ በርካታውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ የዜጎችን የአገልግሎት እርካታ ጨምሯል።
በአሁኑ ወቅትም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ፣ ደሴ እና በሌሎች ከተሞች ላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሥራ ጀምረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት በዘመናዊ አገልግሎት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የምታከናውነው ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በቀጣይም ማዕከሉን በሁሉም አካባቢዎች ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስቀር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መሥራት ይገባል።