‘‘ዲጂታል ለልህቀት'’ በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት የሞባይል መተግበሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገራችን የኢትዮጵያ በሙስና የተተበተበ፣ ኋላ ቀር፣ ፍጥነት እና ጥራት የጎደለው እንዲሁም ዜጎችን ለእንግልት የዳረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ታሪክ ከመሰረቱ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የኢትዮጵያ የመሶብ ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የማስፋፋት ሥራ በተጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ማዕከላቱን ቁጥራቸውን 70 ማድረስ መቻሉ እጅግ የሚያስደንቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
ከማዕከላቱ በተጨማሪም የተንቀሳቃሽ (የሞባይል) አገልግሎቶችም መጀመራቸውን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በቀጣይ በጀት ዓመት ውስጥም መንግሥት ሁሉንም ዓይነት የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥርዓት ለመቀየር በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።