ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ '‘ዲጂታል ለልህቀት'’ በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ በመገኘት፣ ከተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ ላይ የሚያጣምረውን እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ በይፋ መርቀው ስራ አስጀመሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት፣ ይህ ታላቅ ስኬት ለሀገራችን ከፍተኛ የኩራት ምንጭ ከመሆኑም በላይ በቴክኖሎጂ የሚመራ እና ዓላማ ተኮር ኢንቨስትመንት ምን ሊያስገኝ እንደሚችል ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

"መሶብ" የተሰኘው ይኸው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወሳኝ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መተግበሪያው የዜጎችን ጊዜ እንደሚቆጥብ፣ የሙስና ቀዳዳዎችን እንደሚደፍን፣ እንዲሁም በመንግሥት በኩል የተቋማትን ታማኝነትና ጥንካሬ እንደሚያጎለብት አስታውቀዋል።
አያይዘውም ይህ ስኬት ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ትልሞች ተራ ምኞት ብቻ ሳይሆኑ፣ በራሳችን እጆችና አቅም የምንገነባቸው እውነታዎች መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ምስክር መሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ስኬት ይበልጥ በማጠናከር፣ የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ ለአፍሪካውያን ወንድሞች እና እህቶች በማካፈል፣ እንዲሁም ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ አገራዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።