ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የማጠቃለያ ውጤት በግልጽ ያሳያል። "በእርግጥ ይህ ምርጫ ምን ትርጉም አለው?" ለሚለው ጥያቄ፣ ማዕከላዊው ምላሽ የሚገኘው በውጤቱ ውስጥ በተንጸባረቀው የሕዝብ ተሳትፎ፣ የፖለቲካ ብዝኃነት እና ሥርዓቱ ባሳየው አካታችነት ላይ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የማጠቃለያ ውጤት መሠረት፣ በጠቅላላ ምርጫው ከተወዳደሩት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 17ቱ ብሔራዊ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት ችለዋል። ከፓርቲዎች ባለፈ 8 የግል ዕጩዎች አሸንፈው ወደ ምክር ቤት መግባታቸው የዘንድሮውን ምርጫ ልዩ ያደርገዋል።

በተጨማሪም ምርጫው ለግል ዕጩዎች ምቹ የውድድር ሜዳ የፈጠረ ነበር።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር
የዚህ ምርጫ ውጤት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በዋናነት በሚከተሉት ዐበይት ጉዳዮች ላይ ይገለጻል፦
1. የሀሳብ ብዝኃነትን ተቋማዊ ማድረግ (Institutionalizing Pluralism)
ከዚህ ቀደም የነበሩ የፖለቲካ ምህዳር ጥበቶችን በመስበር፣ 17 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና 8 የግል ዕጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወከላቸው፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ 10፣ በአማራ 9፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በሶማሊ ክልል 7 የተለያዩ ፓርቲዎች በክልል ምክር ቤቶች መግባታቸው የሀሳብ ብዝኃነትን በተግባር አረጋግጧል። ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምፅ የሚሰማበትን መድረክ መፍጠር ወሳኝ ነው።
ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ እና በሕግ አውጪው ምክር ቤት ውስጥ በክርክር መፍታት የሰለጠነ ዴሞክራሲ መገለጫ ነው።
2. የታችኛው እርከን የፖለቲካ አካታችነት እና መረጋጋት
በሶማሊ ክልል የኦጋዴን ነፃነት ግንባር (20) እና ነፃነትና እኩልነት (13)፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ኢዜማ (27)፣ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (14) መቀመጫዎችን ማግኘታቸው የዴሞክራሲው መሠረት ከታች ወደ ላይ እያደገ መምጣቱን ያሳያል። ሕዝቡ በልዩነት ውስጥ ያለን ውበት ለመቀበል ያለው ዝግጁነት የሀገራችንን ውስጣዊ አንድነትና ሰላም ያጠናክራል። የዜጎች ጥያቄ በሕጋዊ ተወካዮቻቸው በኩል ምላሽ ሲያገኝ የሀገር ውስጥ ጸጥታና መረጋጋት (National Security and Stability) ይረጋገጣል።
3. የሕዝብ አመኔታ እና ሉዓላዊ ሥልጣን
በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ከ94 በመቶ በላይ የመራጮች ተሳትፎ መመዝገቡ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ጽኑ እምነት ያሳያል። ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥት የሚገነባው የሕዝብ ሉዓላዊ ሥልጣን በምርጫ ካርድ ሲረጋገጥ ነው። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ሰፊ የተፎካካሪዎች ተሳትፎ በተቻለ መጠን ገለልተኛና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር መቻሉ የኢትዮጵያን ተቋማዊ አቅም ከፍ ያደረገ ነው።
4. የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት አቅም (Diplomatic Leverage)
አካታች የሆነና በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ምርጫ ማካሄድ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላትን ገጽታ በእጅጉ ያጎላዋል። መንግሥት ለዲሞክራሲ ግንባታ ያሳየው ከፍተኛ ቁርጠኝነት እና የተፎካካሪዎች ሰላማዊ ተሳትፎ፣ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ ላይ ያላትን የድርድር አቅም እና ብሔራዊ ክብር ከፍ የሚያደርግ ነው።
በአጠቃላይ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት "በእርግጥም ኢትዮጵያ አሸንፋለች!" የሚለው የሚገባው ነው። የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች የአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ የሚሰበሰቡባቸው ሳይሆኑ፣ የተለያዩ የሕዝብ ጥያቄዎችና አማራጭ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው የውይይት መድረኮች እንዲሆኑ በሩ ወለል ብሎ ተከፍቷል።
ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛውን መቀመጫ ቢያገኝም፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅ ጎልቶ መውጣት ኢትዮጵያ የብዙኃን ድምፅ የሚደመጥባት፣ ለጠንካራ ፌዴራላዊ ሥርዓትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለው ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ ምርጫ ኢትዮጵያ በፅናትና በተስፋ፣ ልዩነቶቿን ይዛ በአንድነት ወደፊት እየተራመደች መሆኗን ለዓለም ያወጀ ታላቅ የዴሞክራሲ ድል ነው። አዲሱ የፖለቲካ ምኅዳር ሀገራችንን በሁለንተናዊ መስክ ይበልጥ እንድትበለጽግ የሚያደርጋት የጸና መሠረት ነው።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ