Search

የ5ቱ ዓመት ገጾች፡- የመግባባት ዴሞክራሲ ከፖለቲካዊ ስብራት ጥገና ወደ ተቋማዊ ስኬት

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 55

የመግባባት ዴሞክራሲ ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ዘመናዊ የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን ወደ ተግባር የተቀየረ ተጨባጭ መድኃኒት መሆኑን አሳይቷል።

ለረጅም ዘመናት በጽንፈኛ ርዕዮተ-ዓለሞችና በጥላቻ ፖለቲካ ስትታመስ ለኖረችው ሀገር የመደመር መንግሥት ቁልፍ መፍቻ የሆነውን ሀገር በቀል ሞዴል ይዞ መጥቷል። ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገባቸው ስኬቶች የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል።

ይህ የለውጥ ምዕራፍ የቆዩትን የመገፋፋትና የሴራ ፖለቲካ ባህሎች በመስበር፣ በውይይትና በማካተት ላይ የተመሠረተ አዲስ አሰባሳቢ ትርክት በተግባር የገነባበት የሥራ ዘመን ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገቡት አስደናቂ ስኬቶች መካከል ዋነኛውና ታሪካዊው እርምጃ የተፎካካሪ ፖለቲካ ኃይሎችን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የማካተት ልምድ ነው።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ እንዲመደቡ መደረጉ፣ ፖለቲካን «አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ ከሚወስድበት» አጥፊ አካሄድ ወደ «አጋርነትና የጋራ ኃላፊነት» መድረክነት ቀይሮታል።

ከ64 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ምኅዳር መፈጠሩም ባለፉት ዓመታት መድብለ-ፓርቲ ሥርዓትን ለማስፈን የተደረገው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ያሳያል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተቋማት የደረሱበት የነፃነትና የገለልተኝነት ደረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት የታየ ትልቅ የስኬት ማማ ነው።

እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሚዲያና የፍትሕ ተቋማት ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ተላቀው በገለልተኝነት እንዲሠሩ የተደረገው መዋቅራዊ ማሻሻያ ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

እነዚህ ተቋማት ዜጎች መብታቸውን በብሔርና በባህል ማዕቀፍ ብቻ ሳይሆን በሕግና በዜግነት ደረጃ እንዲጠይቁና እንዲያስከብሩ አቅም ፈጥረዋል።

ይህ የመግባባት ዴሞክራሲ ሞዴል ከውጭ የመጡ ርዕዮተ-ዓለሞችን በጭፍን ከመቅዳት ይልቅ በሀገር በቀል ዕውቀትና በኢትዮጵያ ታሪካዊ ሥነ-ልቦና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፎችም አበረታች ውጤቶችን ለማስመዝገብ አስችሏል።

የግለሰብና የቡድን መብቶችን ሚዛን በመጠበቅ፣ ጽንፈኝነትን በማስወገድና ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አሰባሳቢ ትርክት ላይ በማተኮር ሀገራችን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር ማምጣት ተችሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኙት እነዚህ ተጨባጭ ስኬቶች የመግባባት ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልጽግና የሚያረጋግጥና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።

በበረከት ሽመልስ