ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቀጣዩ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል።
በሀገራችን በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ም/ቤቶች መቀመጫን በማግኘት ማሸነፉ በትላንትናው እለት ተገልጿል።
ከዚህ ባሻገር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት መቀመጫ ማግኘታቸው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል ።
ይህም በምክር ቤቶቹ ውስጥ የሀሳብ ብዝሃነት እንዲሰፍንና አማራጭ ሀሳቦች እንዲደመጡ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላይ አዲስ አቅጣጫ ማሳየቱ ተገልጿል።
ይህም የሀገራችን የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት ከአንድ ወገን የፖለቲካ የበላይነት ወደ ብዝሀ-ሐሳብ ሥርዓት እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳይ ጉልህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ሲሉ የአለምአቀፍ ህግ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ታደሰ ተናግረዋል።
ይህ ስብጥር በተቋማዊ መድረኮች ላይ አማራጭ ፖሊሲዎች፣ ገንቢ ትችቶች እንዲሁም የተለያዩ ማህበራዊ ፍላጎቶችና ሕዝባዊ ጥያቄዎች በሰፊው እንዲስተናገዱ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ይህም በቀጣይ የሚደረጉ የምክር ቤት ውይይቶችን ይበልጥ አካታች፣ ተመጣጣኝና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው እንደሚያደርጋቸው ይጠበቃል ብለዋል ።
አቶ ጌታቸው ለኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እንደገለጹት ከተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የመጡ አካላት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በምክር ቤቶች ውስጥ ውክልና ማግኘታቸው፣ የሕዝብን በሀገራዊ ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ ለማጎልበትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም የሃሳብ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የፖለቲካ መዋቅር ለመፍጠር የገባውን ቃል በመተግበር ረገድ ይህ የምርጫ ውጤት ትልቅ እርምጃ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው ሂደቱ የሀገራችንን ፖለቲካ ከግጭት ወደ ውይይት፣ ከመጣላት ወደ መደማመጥ፣ እንዲሁም ከማግለል ወደ ተሳትፎ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የተለያዩ ድምፆች ወደ ምክር ቤቶቹ መግባታቸው የተለየ የፖሊሲ አማራጭ ሃሳብ በአደባባይ እንዲደመጥ በር የሚከፍት ሲሆን ለስልጡን የፖለቲካ ባህል ግንባታ፣ ለሰላማዊ ፉክክር፣ ለሃሳብ መቻቻል እንዲሁም ሕዝቡ በዲሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ያለውን እምነት ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
በቤተልሔም ገረመው