Search

በብዝኃ ድምፅ የጸናችው ኢትዮጵያ፤ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ታሪካዊ ማኅተም

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 60

ኢትዮጵያ የብዙ ቀለማት፣ የብዙ ቋንቋዎችና የብዝሀ ሀሳቦች ማኅደር ናት። ይህንን ውብ የተፈጥሮ ስብጥር ወደ ፖለቲካዊ ሥርዓት በመቀየር ረገድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።

May be an image of lighting, table and wedding

ይህ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተለየ መልኩ በምርጫው ከተሳተፉት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 17ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፋቸው፣ የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የራሱን ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው።

ይህም የብልፅግና ፓርቲ ያገኛቸውን 438 መቀመጫዎች ጨምሮ፣ እንደ ኢዜማ (13 መቀመጫዎች)፣ አብን (6 መቀመጫዎች)፣ መድረክ (3 መቀመጫዎች)፣ አዴኃን (3 መቀመጫዎች) እና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (3 መቀመጫዎች) ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በሕዝብ ተመርጠው ድምፅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ይህ የውጤት ስብጥር የሚያሳየው ትልቁ እውነት፣ የኢትዮጵያ የፓርላማ ብዝሀ ድምፅ የሚደመጥበት እድል መስፋቱን ነው።

ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጀምሮ፣ ኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ ሱማሌ ፌደራሊስት፣ ኀብረት ለዴሞክራሲ፣ የጉሙዝ ሕዝብ፣ አርጎባ አንድነት፣ የአፋር ሕዝብ፣ አዲስ ትውልድ፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ የዎላይታ ሕዝብ እና የጌዴኦ ሕዝብ ድርጅቶች እያንዳንዳቸው መቀመጫ ማግኘታቸው፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ልዮ ልዮ ቀለም ያላቸው ድምፆች በከፍተኛው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ጎልቶ እንዲሰማ ዕድል የፈጠረ ልዩ የታሪክ ዐሻራ ነው።

በተጨማሪም 8 የግል ዕጩዎች ማሸነፋቸው የሥርዓቱን አካታችነት ይበልጥ ያጠናክረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ታሪካዊ ምርጫ አካታች ለማድረግ የሄደበት ርቀትና የተጠቀመበት ቴክኖሎጂ ለሂደቱ ስኬት ትልቅ ምሰሶ ነበር።

በምርጫው ዋዜማ የተካሄዱት 19 የፖሊሲ ክርክሮች የሀሳብ ፍልሚያ እንጂ የኃይል አማራጭ እንደማያዋጣ ያሳዩ ነበሩ። ከ1 ሺህ 800 በላይ የሀገር ውስጥና 45 የውጭ ጋዜጠኞች በነፃነት እንዲዘግቡ መደረጉም የሂደቱን ግልፅነት ለዓለም ህዝብ መስክሯል።

ያጋጠሙ ችግሮችና እክሎች በ663 አባላት ባሉት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችና በሕጋዊ መንገዶች ለመፍታት የተደረገው ጥረት፣ የኢትዮጵያ ተቋማዊ አቅም መጎልበቱንና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲ እየተገነባ መሆኑን ያሳያል።

በአጠቃላይ ፣ የዘንድሮው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት የሚያረጋግጠው፣ የኢትዮጵያ ፅናት በብዙሃን ድምፆች መከበርና መደመጥ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው። የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ማሸነፍ ለነገዋ የበለፀገችና የተረጋጋች ኢትዮጵያ የጸና የመሠረት ድንጋይ ነው።

ይህ የብዙሃን ኅብረ-ዜማ የተሰማበት ምርጫ ሀገራችን በዲሞክራሲ ጎዳና ላይ ወደፊት እንድትራመድ የሚያደርጋት የታሪክ ብርሃን ሆኖ ይኖራል። ተቃራኒ ሀሳቦች በመድረክ ላይ ሲፋጠጡ እንጂ በጦር ሜዳ ሲታኮሱ ሀገር አትገነባምና፣ ይህ የውይይትና የሕግ የበላይነት ድል ለሁላችንም ትልቅ ትርጉም አለው።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ