Search

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ“አራዳ የበጎነት መንደር“ ግንባታን አስጀመሩ

ሰኞ ሰኔ 15, 2018 74

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከከንቲባ ፅሕፈት ቤት ጀርባ የሚገኘውን የ“አራዳ የበጎነት መንደር“ ግንባታን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

No photo description available.

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፅ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የመረጠንን ህዝብ የምናመሰግነው በቃላት ብቻ ሳይሆን ችግሩን የሚፈቱ ተጨባጭ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በትናንትናው እለት በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በተጣለባቸው የህዝብ እምነት ዳግም ኢትዮጵያን ለመምራት ተጨማሪ አምስት ዓመት ለፓርቲያቸው ብልፅግና በተሰጠበት ማግስት፣ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እጅግ የተጎሳቀሉና ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶችንና አካባቢውን ወደ ንጹህና ውብ መንደር ለመቀየር ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት መጀመራቸውን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በአጠቃላይ 2 ሺህ 500 ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፣ ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የ“አራዳ የበጎነት መንደር“ ባለ 9 ወለል 8 ህንፃዎች እና ሁለት ባለ 4 ወለል የገበያ ማዕከላት ያሉት ሆኖ ለሰው ልጆች ምቹና ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥር እንዲሁም የከተማዋን ውበት የሚቀይር መንደር ሆኖ ይገነባል።

ይህ መንደር የተጎሳቆሉ ቤቶችንና አካባቢዎችን በመቀየር ለኑሮ ምቹና ንጽሕናቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶች፣ የጋራ መገልገያዎች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች እና ሕፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸው የስፖርት ሜዳዎችን የሚያካትት ነው።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው በክረምት በጎ ፍቃድ ቤት ከመገንባት ባለፈ አካባቢን የማጽዳት፣ የጎርፍ መከላከያዎችን የመስራት፣ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ማዕድ የማጋራት፣ የደም ልገሳ የማካሄድ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞችን የመትከል፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት፣ የነፃ ሕክምና አገልግሎት የመዘርጋትና የትራፊክ ፍሰትን የማሳለጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

No photo description available.

በእነዚህ ተግባራት የሚገነባው መተማመንን፣ ጽናትን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን/እህትማማችነትን ሲሆን ይህም በጥቅሉ የኢትዮጵያ የብልፅግና መንገድ ነው።

በመጨረሻም የከተማዋ ባለሀብቶች ለህዝብ አኗኗር መለወጥ ለሚደረጉ ጥሪዎች ሁሉ ቀናና ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው ያመሰገኑት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ዛሬ ግንባታው ለተጀመረው መንደር እያንዳንዳቸው አንድ ባለ 9 ወለል ህንፃ ለመገንባት ቃል ለገቡት ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለበላይነህ ክንዴ እና ለያደታ ጁነዲን እንዲሁም በጋራ ለመገንባት አብረዋቸው ለቆሙት ለቲኤንቲ ኮንስትራክሽን፣ ለግራንድ ሌጋሲ ሃውስ፣ ለኢቲ ኦንላይን ኮሌጅ፣ ለአብይ ማስረሻ፣ ለዴማ ሪልስቴት፣ ለቴምር ሪልስቴት፣ ለስናፕ ትሬዲንግ፣ ለጊፍት ሪልስቴት፣ ለመሃመድ አድናን እና ለአሚር በድሩ በነዋሪዎችና በራሳቸው ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።