ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት አመራሮች በተገኙበት በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሀገራዊ ምክክሩ የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦችን እና ምክረ ሐሳቦችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌዴራል እና ለክልል መንግሥታት በይፋ አስረክቧል።
ይህ የሰነድ ርክክብ፤ በምክክርና በሰላማዊ መንገድ የኢትዮጵያን የቆዩ ሀገራዊ ፈተናዎች መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፤ በመደመር መንግሥት ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ የተበጀለትን የሀገራዊ ምክክር ሂደት አንድ ትልቅ ምዕራፍ ያበስራል።
ሂደቱ ለውይይት፣ ለጋራ መግባባት እና ስምምነትን ለመፍጠር የሚያስችል አካታች መድረክ መመሥረቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል።
ባለፉት አራት ዓመታትም ይህ ሂደት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ችሏል። ተሳታፊዎች ባደረጓቸው ሰፊ ምክክሮች እና በተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አማካኝነት ዕይታዎቻቸውን ለማንጸባረቅ፣ ልዩ ልዩ አመለካከቶችን ለመስማት እና የጋራ መግባባት የተደረሰባቸውን መስኮች ለመለየት ዕድል ማግኘታቸው ተጠቁሟል።
የእነዚህ ውጤቶች በይፋ መቅረብ በምክክሩ የተሰበሰቡ እይታዎችን እና የውሳኔ ሐሳቦችን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተቀየሰ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: