Search

ዓባይን የበረሃ ሲሳይ የሚያደርገው የግብፅ ስግብግብነት እና የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የልማት ከፍታ፦ ቶሽካ

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 82

በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የቀጠለው የግብፅ "የውኃ ስጋት ትርክት" መሬት ላይ ካለው እውነታ በእጅጉ ይቃረናል።

ግብፅ ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች በመቃወም የምታቀርበው ክስ በሳይንሳዊ እና ሃይድሮሎጂካዊ ማስረጃዎች ፊት ሚዛን የሚደፋ አይደለም።

የዓለም አቀፍ ጥናቶች መረጃ እንደሚያረጋግጠው በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ ላለው የውኃ እጥረት ስጋት ዋናው ምክንያት የላይኛው ተፋሰስ ልማት ሳይሆን፣ ግብፅ በሰሃራ በረሃ ውስጥ የምታባክነው ግዙፍ የውኃ መጠን ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃይድሮሎጂ ጥናቶች መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአስዋን ግድብ ሰፊ የውኃ አካል እና በከፍተኛ የበረሃ ሙቀት ምክንያት ብቻ ግብፅ በየዓመቱ ከ10 እስከ 16 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት ውኃ በትነት ታባክናለች።

ይህ ግዙፍ የውኃ ብክነት ግብፅ በምዕራባዊ ክፍሏ በረሃማ አካባቢ በሚገኘው የቶሽካ ፕሮጀክት በኩል የምታባክነውን አይጨምርም።

የቶሽካ ፕሮጀክት የዓባይን ውኃ ከናስር ሐይቅ በመውሰድ ወደ ምዕራባው በረሃ በማፍሰስ ለእርሻ ልማት ለማዋል የተነደፈ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

በዚህ የቶሽካ ፕሮጀክት አማካኝነት የሚንቀሳቀሰው የውኃ ማስተላለፊያ ሥርዓት በየዓመቱ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ንጹህ የዓባይን ውኃ ከአስዋን ሐይቅ እየሳበ ወደ ሰሃራ በረሃ ይለቅቃል።

በበረሃው በከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት እና በክፍት ቦዮች ምክንያትም በቶሽካ አካባቢ በተፈጠሩት ሰው ሠራሽ ሐይቆች ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ በጥቅም ላይ ሳይውል በአየር ላይ ይተናል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቶሽካ ፕሮጀክት አካባቢ ያለው የውኃ ትነት መጠን በአስዋን ግድብ ካለው የትነት መጠን እጅግ የላቀ በመሆኑ የውኃ ብክነቱን በእጅጉ ያባብሰዋል።

የሃይድሮሎጂ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ካይሮ ይህንን በበረሃ ላይ በከንቱ የሚባክን ግዙፍ የውኃ መጠን በዘመናዊ የውኃ አጠቃቀም እና ቁጠባ ቴክኖሎጂዎች ማስተዳደር ብትችል ኖሮ፣ ምንም ዓይነት የውኃ እጥረት ስጋት አይኖርባትም ነበር።

ነገር ግን የካይሮ ባለሥልጣናት ይህንን በሳይንስ የተረጋገጠ የውኃ ቁጠባ መፍትሔ ከመተግበር ይልቅ ውኃን በበረሃ ላይ እያባከኑ ሌሎችን መክሰስ መምረጣቸው ለፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም የተዘጋጁ አለመሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።

የግብፅ ዋና ችግር የውኃ እጥረት ሳይሆን የውኃ ሀብቱን በብቸኝነት የመቆጣጠር እና የቅኝ ግዛት ዘመን ፍላጎትን የመጫን የቆየ ፖሊሲ ነው።

በአንፃሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዓባይን ውኃ ለትነት በማያጋልጥ አካባቢ የተገነባ በመሆኑ የውኃ ብክነትን የሚከላከል ፕሮጀክት መሆኑን ሳይንስ አረጋግጧል።

የሕዳሴ ግድብ አካባቢ የትነት መጠን ከአስዋን ግድብ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ለተፋሰሱ ተጨማሪ ውኃ እንዲገኝ የሚያደርግ ነው።

ግድቡ የዓባይን የውኃ ፍሰት ዓመቱን ሙሉ በማመጣጠን በአስዋን ግድብ ላይ ይባክን የነበረውን ከፍተኛ የውኃ ትነት በመቀነስ ለተፋሰሱ ተጨማሪ የውኃ ሀብት እያስገኘ ይገኛል።

ይህ ሳይንሳዊ እውነት የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያ ልማቷን ስታካሂድ የትኛውንም የተፋሰሱን ሀገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት እና ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ በተግባር እንደምትከተል ነው።

ግብፅ በገዛ ግዛቷ ከፍተኛ መጠን ያለውን የዓባይ ውኃ በበረሃ ላይ በከንቱ እያባከነች፣ ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ላይ የምታሰማው ተደጋጋሚ ተቃውሞ ከውኃ ደኅንነት ስጋት የመነጨ አይደለም።

ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን ልማት እና ዕድገት አለመቀበል እና በልማቷ ላይ እንቅፋት የመፍጠር ከንቱ ፍላጎት ማሳያ ነው።

ሆኖም #ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ፣ እውነተኛ የውኃ ደኅንነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በፖለቲካዊ ውዥምብር ሳይሆን በሳይንሳዊ የውኃ አስተዳደር እና በፍትሐዊ የትብብር ማዕቀፍ ላይ በመመስረት እንደሆነ በተግባር እያሳየች ነው።

በመሆኑም የካይሮ ከንቱ ሩጫና ሴራ የኢትዮጵያን የማይገታ የከፍታና የልማት ጉዞ ፈፅሞ ሊያስቆመው አይችልም።

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: