በወላይታ ዞን ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ትላንት ከሰዓት በኃላ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት ምክንያት የ3 ሰዎች ሕይወት አለፈ።
የሦስቱ ሰዎች ህይወት ያለፈው በወረዳው ባለዉ በፍንጫዋ ፏፏቴ አጠገብ ሣር አጨዳ ላይ በነበሩበት ወቅት በተከሰተዉ የመሬት መንሸራተት አደጋ መሆኑን ዞኑ አስታውቋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማቹ ሶርሳ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት አደጋው በአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን፣ የአስክሬን ፍለጋ በስፍራው እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ስዓት ድረስ የአንዲት ሴት አስክሬን መገኘቱን ተናግረዋል።
አካባቢው ለናዳ እና መሬት መንሸራተት ተጋላጭ መሆኑን ያሰረዱት ኃላፊው፥ የአካባቢው ነዋሪዎች የክረምት ዝናብ ተጨማሪ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተመስገን ተስፋዬ