የኢትዮጵያ መሪዎች በየዘመናቱ የየራሳቸውን ታሪክ ትተው ሄደዋል።
ኢትዮጵያውያንም በአንድነት እና በኅብረት በቆሙበት ሁሉ የጀግንነት ታሪካዊ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል።
የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አበባው አያሌው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ከቀደምት የዓለም ስልጣኔዎች ተርታ የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በሺህ ዘመናት ታሪኳ በአንድነት እና በኅብረት በመቆም በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ መቻሏን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያውያን የድል ታሪክ በሙሉ በአንድነት የመቆም ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን፣ የአክሱም ሐውልቶችን፣ የጎንደር አብያተ መንግሥትን፣ የጢያ ትክል ድንጋችን እና የኮንሶ የእርከን ሥራን የመሳሰሉ የዘመናት ጥበብ የሚገለጥባቸው ሥራዎችን ማከናወን መቻላቸውን በአብነት አንስተዋል።
የታሪክ ተመራማሪው አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ከጥንታዊ የስልጣኔ አሻራዋ ባሻገር በሀገሪቱ ያለው የተለያየ ባህል እና ቋንቋም ራሱን የቻለ ሐብት መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ ትውልድ የቀደምት አባቶቹን አርበኝነት በመከተል በራሱ ጥረት ሕይወቱን ማሻሻል፣ በሀገራዊ ልማትም የራሱን ዐሻራ ማሳረፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ከድህነት በመላቀቅ የተሻለች ሀገር ለመገንባትም ወጣቱ በአንድነት በመቆም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ