ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ‘ኑክሌር’ የሚለውን ቃል ሲሰማ ወደ አእምሮው የሚመጣው ፍርሃት እና እጅግ አውዳሚ የሆነ ኃይል ብቻ ነበር።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥሎት የሄደው አስፈሪ ምስል ከሰው አእምሮ ሳይደበዝዝ፣ እንዲሁም በሄሮሺማ እና ናጋሳኪ የተከሰተው እልቂት፣ የኑክሌርን ጎጂነትን እንጂ ጠቃሚ ጎንም ሊኖረው እንደሚችል እንዳይታሰብ አድርጎታል።
ሁኔታዎች በዚህ መልኩ እንዳሉም ይህን ጭጋጋማ ምስል መሸፈን የቻለ እና የኑክሌርን ሌላ ገጽታ የሚያሳይ እውነታ ተሰማ።

ከሞስኮ በስተደቡብ ምዕራብ በምትገኘው አብኒንስክ በምትባለው ትንሽ ከተማ የተሰባሰቡ የሶቪየት ሳይንቲስቶች በአብዛኛው ሰው አእምሮ የተሳለውን አንድ-ወጥ የኑክሌር ግንዛቤ ለዘለቄታው ቀየሩት።
የአብኒንስክ ኑክሌር ጣቢያ በዋነኛነት የተቋቋመው የኑክሌር ኃይልን ለሰላማዊ አገልግሎት ማዋል እንደሚቻል ለማሳየት እና በዘርፉ ተመሳሳይ ምርምር እያካሄዱ ከሚገኙ ሀገራት በቴክኖሎጂው ቀድሞ ለመገኘት ነበር።
ይህንን እውን ለማድረግም በኑክሌር ሳይንቲስቱ ኢጎር ኩርቻቶቭ የሚመራው የኑክሌር ጠቢባን ስብስብ እ.አ.አ በ1951 ሥራውን ጀመረ።

ይህን መሰል ውስብስብ እና ረቂቅ ስሌቶችን የመሥራት ብቃት ያለው የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ባልነበረበት በዚያን ወቅት የሶቪየት ሳይንቲስቶች የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ለመከወን ብዙውን የረቀቁ ስሌቶች በሰው አእምሮ ብቻ ያከናውኑ ነበር።
በዚህ መልኩ ብዙ ሃብት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል በመጠቀም ሲሠራ የነበረው የዓለማችን የመጀመሪያው ሰላማዊ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ከሦስት ዓመት ተኩል የግንባታ ጊዜ በኋላ እ.አ.አ ሰኔ 27 ቀን 1954 ሥራው ተጠናቅቆ ከዓለማችን የመጀመሪያው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ የተገኘው ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት እንዲገባ ተደረገ።
ይህ ዕለትም የሰው ልጅ ኑክሌርን ከአውዳሚነቱ በተቃራኒ ለዕድገት ለማዋል እንቅስቃሴ የጀመረበት ታሪካዊ ምዕራፍ ሆነ።

ይህ በወቅቱ የረቀቁ ዘመናዊ ኮምፒዩተሮች በሌሉበት በእጅ ስሌት እና በሰው ልጆች የላቀ ችሎታ በተግባር ላይ የዋለው የአብኒንስክ ኑክሌር ጣቢያ ዛሬ ካሉት ትላልቅ የኑክሌር ኃይል ጣቢያዎች አንፃር የሪአክተሩ የማመንጨት አቅም 5 ሜጋ ዋት ብቻ ቢሆንም አውዳሚውን ኃይል ለሰላማዊ አገልግሎት ማዋል እንደሚቻል ያሳየ በመሆኑ በታሪክ ትልቅ ቦታ የያዘ ታሪካዊ መሠረተ ልማት ነው።

ከዚህም ባለፈ ሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ ዘርፍ በኑክሌር ኃይል ዘርፍ ምርምር እንዲያደርጉ በር ከፍቷል።
በዚህ መልኩ ጥቅም ሲሰጥ የቆየው ታሪካዊው የሩሲያ ኑክሌር ጣቢያ አብኒንስክ ለ48 ዓመታት ያህል ያለምንም አደጋ እና ያለምንም የጨረር ልቀት በአስተማማኝ ሁኔታ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

በኋላም በእርጅና ምክንያት የሚያመነጨው ኃይል እያደር እየቀነሰ መምጣት እንዲሁም ለእድሳት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ እ.አ.አ በ2002 በይፋ ተዘግቶ ወደ ሙዚየምነት ተቀይሮ በመጎብኘት ላይ ይገኛል።
በዋሲሁን ተስፋዬ