Search

11ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋፅኦ የምታፀናበት ነው - አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 68

11ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋፅኦ የምታፀናበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገለጹ።

ከጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው 11ኛው ጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ለሶስት ቀናት የሚመክር ይሆናል።

ፎረሙ በአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በመምከር መፍትሔ አመላካች ምክረ ሐሳቦች የሚቀርቡበት አህጉራዊ መድረክ መሆኑን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ የመንግስት አካላት፣ ሚኒስትሮች፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል።

የዘንድሮው የጣና ፎረም አፍሪካ በተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ የሚኖራትን ሚና እንደሚዳስስ አምባሳደር ነቢያት አንሥተዋል።

ወቅታዊው የዓለም ሁኔታ የፖለቲካ ፉክክር እየከረረ እና የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ትብብር እየላሉ የመጡበት መሆኑን አስረድተዋል።

በጣና ፎረም አፍሪካ ውጥረት በተሞላበት ዓለም አቀፍ ሁኔታ የሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ያሏትን መፍትሔዎች እንደምታራምድ አብራርተዋል።

የጣና ፎረም ትኩረት አፍሪካዊ መፍትሔዎች ላይ ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፣ በዚህም ከአፍሪካውያን የመነጩ የሰላም እና ደኅንነት የመፍትሔ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመድረኩም ለአፍሪካውያን የፖሊሲ አውጪዎች ምክረ ሐሳብ የሚሆኑ ሐሳቦች የሚወጡበት መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ተሳታፊ ሙያተኞች በአፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮች እና በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ልምድ እና ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ዝግጅትም ተጠባቂ የፎረሙ የመርሐ ግብር አካል ነው።

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Africa #TanaForum