Search

በአማራ ክልል ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሠበሰበ

ሓሙስ ጥቅምት 27, 2018 42

በአማራ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን በተለያየ ሰብል ከለማው መሬት ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሠብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ቀድሞ የደረሰውን ሰብል ፈጥኖ በመሠብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብና ከብክነት የመከላከል ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ ከለማው ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እስካሁን 1 ሚሊዮን 240 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሠብሰቡን ለኢዜአ አስታውቀዋል።
የተሰበሰበው ሰብልም ቀድሞ የደረሰ የገብስ፣ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የቦሎቄ፣ የማሾ፣ የአተር፣ የማሽላና የጤፍ ሰብል መሆኑን አስረድተዋል።
 
የምርት ብክነትን ለመከላከል ቀድሞ የግንዛቤ ሥራ በመፍጠር ሰብሎችን በጥንቃቄ የማጨድ፣ የመከመርና የመውቃት ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽም አርሶ አደሩ ቤተሰቡን በማሰማራት፣ በኮምባይነርና አነስተኛ የሰብል መውቂያ ማሽኖችን በመጠቀም እንዲሰበሰብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብሉን ፈጥኖ በመሠብሰብ ለቀሪ እርጥበትና ለበጋ መስኖ መሬቱን እንዲያዘጋጅ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መልካሙ በዜ በሰጡት አስተያየት፤ ግማሽ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ያለሙትን ገብስ ወቅቱን ጠብቀው መሠብሰባቸውን ተናግረዋል።
የደረሰውን ሰብል ቀድመው መሰብሰባቸው ቀሪ እርጥበትን በመጠቀም በዳግም ሰብል ልማት ሽምብራ እየዘሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በግማሽ ሄክታር መሬት ያለሙትን ገብስ አጭደው መሠብሰባቸውን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን በሰከላ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት አንማው ጋሹ ናቸው።
ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል በ2017/2018 የምርት ዘመን ከለማው መሬት ከ187 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።