Search

ኢትዮጵያ እየተሳተፈችበት ያለው 2ኛው የዓለም ማኅበራዊ ልማት ጉባዔ ዓላማ ምንድን ነው?

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 30

2ኛው የዓለም ማኅበራዊ ልማት ጉባዔ በኳታር ዶሃ እየተካሄደ ይገኛል። የዚህ ጉባዔ መነሻው እአአ በ1995 በኮፐንሀገን የተካሄደው የመጀመሪያው የማኅበራዊ ልማት ጉባዔ ነው።
እአአ በ2000 ደግሞ የኮፐንሀገኑ ጉባዔ የአምስት ዓመት ግምገማ (WSSD+5) በጄኔቫ ተካሂዷል። አሁን በዶሃ እየተካሄደ ያለው ጉባዔ መነሻውን የኮፐንሀገን ጉባዔ ስለሆነ እና የ30 ዓመት ግምገማ በመሆኑ ነው "2ኛው የዓለም ማኅበራዊ ልማት ጉባዔ" የሚባለው።
የኮፐንሀገን ጉባዔ 10 የማኅበራዊ ልማት ቃል ኪዳኖችን በዝርዝር አስቀምጦ ነበር። እነዚህም ሁለንተናዊ ፍትሐዊነትን ማስፈን፣ ድህነትን ማስወገድ፣ የተሟላ የሥራ ዕድልን መፍጠር፣ ማኅበራዊ ውህደት ማፋጠን፣ የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ ሁለንተናዊ የትምህርት እና የጤና ዕድልን ማስፋት፣ የተፋጠነ ልማት፣ መዋቅራዊ ማስተካከያ ተግባራዊ ማድረግ፣ ሀብት ማሰባሰብ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ናቸው።
ትናንት የተጀመረው የዶሃው ጉባዔ እስከ ነገ (ከኖቬምበር 4 እስከ 6 ቀን 2025) የሚካሄድ መሆኑን ከወጣው መርሐ-ግብር ለመረዳት ይቻላል።
የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ በኮፐንሀገን የማኅበራዊ ልማት ጉባዔ ላይ የተገቡ 10 ቃል ኪዳኖች አፈፃፀምን መገምገም እና የትግበራ ክፍተቶችን በመፍታት ለ2030 ዘላቂ የልማት አጀንዳ አዲስ መነሳሳትን መፍጠር ነው።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት መሥራች አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን በ2ኛው የዓለም ማኅበራዊ ልማት ጉባዔ (WSSD2) እየተሳተፈች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ድህነትን በመቀነስ እና ዜጎቿን ወደ ብልጽግና በማሸጋገር ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከማኅበራዊ ልማት ጉባዔው ዋና ዓላማ ጋር ይጣጣማል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሕዝብ ብዛት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ሙሉ እና ውጤታማ የሥራ ስምሪት ለማረጋገጥ እና መደበኛ ያልሆነውን ዘርፍ ከመደበኛና ሥራ ጋር በማዋሃድ ላይ አፅንዖት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። ይህም የዶሃ መግለጫ ዋና ጭብጥ በመሆኑ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ትርጉሙ የላቀ ነው።
እንደ ምርታማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (PSNP) ያሉ መጠነ ሰፊ የማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞችን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ አድርጋለች። በዚህም ጉባዔው ልምዶቿን እንድታካፍል፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተናበበ እና አደጋን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ በመገንባት የማኅበራዊ ጥበቃ ደረጃዋን ከፍ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ትብብርን የምታገኝበት መድረክም ነው።
ጉባዔው ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) በተለይም ከድህነት (SDG 1)፣ ከጤና (SDG 3)፣ ከትምህርት (SDG 4) እና ከሥርዓተ-ፆታ (SDG 5) ጋር በተያያዙ ግቦች ላይ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች የምታቀርብበት ነው።
የአፍሪካ ቡድን እና የታዳጊ ሀገራት (LDCs) ቡድን አባል እንደመሆኗ መጠንም ኦፊሴላዊ የልማት ድጋፍ (ODA) ከፍ ለማድረግ፣ የዕዳ ጫናን ለመቀነስ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዲሰፍኑ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ማስተካከያ እና ማኅበራዊ ልማት ፕሮግራሞች ድጋፍ እንዲያድግ ድምጿን የምታሰማበት መድረክም ነው።
በለሚ ታደሰ