ውጤታማ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓትን በመተግበር የዜጎችን ህይወት የተሻለ ማድረግ ከመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት የመንግሥት ስርዓቶች የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ የኢኮኖሚ ሞዴሎች በመተግበራቸው የሚፈለገውን ያህል እድገት እንዳይመዘገብ አድርጎ ቆይቷል፡፡
በዚህ ረገድ የመደመር መንግስት በኢትዮጵያ ሊተገበር የሚገባው የኢኮኖሚ ሞዴል በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ትብብር የሚሰራ የኢኮኖሚ ሞዴል እንደሆነ ይገልፃል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተፃፈው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ በኢትዮጵያ ሊተገበር የሚገባውን የኢኮኖሚ ስርዓት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
የመደመር መንግሥት እሳቤ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና ትብብርን መሰረት ያደረገ እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡
በዓለም ላይ ሁለት አይነት የኢኮኖሚ ሞዴሎች የሚተገበሩ ሲሆን አንደኛው ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ በግሉ ዘርፍ የሚመራበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚሆንበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንዱን ብቻውን መተግበር ውጤታማ እንደማያደርግ የመደመር መንግስት መፅሐፍ ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ብቻ ኢኮኖሚውን የሚመራ ከሆነ ዘርፉ በካፒታል፣ በአደረጃጀት እና በፈጠራ ገና ያልዳበረ በመሆኑ ውጤቱን የተሳካ እንደማያደርገው የመደመር መንግሥት እሳቤ በምክንያትነት ያስቀምጣል፡፡
መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያልተገራ ጣልቃ ገብነት ካላው የግሉን ዘርፍ እንደሚያቀጭጭ፣ ሙስናን እንደሚያስፋፋ፣ ፈጠራን እንደሚቀንስ እንዲሁም የሰዎችን የሀብት ባለቤትነት እንደሚያሳጣ ካላፉት መንግስታዊ ስርዓቶች በመነሳት የመደመር መንግስት እሳቤ በዝርዝር ያስረዳል፡፡
የመደመር መንግሥት የሚከተለው ሞዴል የእነዚህን ሁለት ፖሊሲዎች ችግር የሚፈታውን የትብብር ሞዴል ሲሆን፤ በዚህ ሞዴል የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ ተገቢውን ሚና ይጫወታል፣ ይደገፋል እንዲሁም ይበረታታል፡፡
መንግስት ደግሞ በስራ ፈጠራ እሳቤ የግሉ ዘርፍ በማይደፍራቸው ዘርፎች ላይ እንዲሳተፍና ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በማልማት፣ አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨት እና አዳዲስ የኢኮኖሚ ዘርፎችን እንዲፈጥር የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ምክረ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
በዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የተቀዱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እና ስርዓቶችን ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሳታጣጥም መተግበሯ የዜጎቿ የኑሮ ደረጃ እንዳይሻሻል አድርጎ መቆየቱን በመደመር መንግስት እሳቤ ውስጥ በዝርዝር ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከእነዚህ ችግሮች ተላቃ ካደጉት ሀገራት ጎራ እንድትቀላቀል በዋናነት ሶስት ስልቶች መተግበር እንዳላባቸው በመደመር መንግስት መፅሐፍ ውስጥ የሰፈሩ ሲሆን፤ እነዚህም ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ዝላይ ናቸው፡፡
በሐይማኖት ከበደ
#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #YemedemerMengist