በጣሊያን እግር ኳስን ባህል ስላደረጉ ተጫዋቾች አብዝቶ በመፃፍ የሚታወቀው ፒተር ማን ባንድ ወቅት ስለፍራንኮ ባሬሲ ለመፃፍ ፈልጎ ከቅርብ ጎደኛው ፓውሎ ማልዲኒ ጋር ቆይታ አደረገ።
ማልዲኒም ስለባሬሲ ተናግሮ ማቆም አልቻለም። "ከእሱ ጋር ዕድል ቀንቶኝ አንድ ላይ ተጫውቻለሁ። ታቃለህ መቆም እንደሱ የሚጠላ ተጫዋች አይቼ አላውቅም። አንዳንዴ የኔን ሀላፊነት ሁሉ ሲወጣ እናደድ ነበር። ለስሙ ለሁለት ተጣመርን እንጂ ብቻውን ነው የሚጫወተው። ከጨዋታ በኋላ ሻወር ስንወስድ እንደተጫወተ ሰው አብረን እንወስዳለን።
ፒተር ማን በሰማው ነገር ተገርሞ መሳቅ ጀመረ። ማልዲኒ ግን መናገር አላቆመም "ጣሊያን እሱንና ታላቅ ወንድሙን ጁሴፔ ባሬሲን በማፍራቷ ልትኮራ ይገባል። በተለይ ሚላን ለዛሬ መቆሟ ያለጥርጥር ምከንያቷ እሱ ነው። በዘመኔ ግን ፍራንኮ ባሬሲን በማየቴ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል።" ሲል ንግግሩን ቋጨ። ጸሃፊው ፒተር ስለ ባሬሲ የሚያውቀውን እና ይበልጥ ከማልዲኒ ያገኝውን ምንም ሳያስቀር በመጽሄት ላይ ካሰፈረው የተወሰደ ነው፡፡
በሙሉ ስሙ ፍራንቺኖ ባሬሲ ይባላል ኤስ ሚላኖች ደግሞ ትንሹ (THE LITTLE ONE) ይሉታል። ውልደትና ዕድገቱ በጣሊያኗ ትራቫሊያቶ ከተማ ሲሆን ከዛሬ 65 ዓመታት በፊት ነበር ወደዚች ምድር የመጣው።

ይህ ሰው ዛሬ ላይ ዓለም ቢመሰክርለትም ትላንት እስከ 10 ዓመቱ ድረስ አንድም ቀን ቴሌቪዥን ተመልክቶ እንኳን አያውቅም። ዝቅተኛ የህዝብ ቁጥር ያለባት የውልደቱ ከተማ የራሱ ቤተሰብን ጨምሮ አብዛኛው ማህብረተሰብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ነው ያለፈባት።
ግን ያ ታሪክ ሆኗል ነው። ጣሊያን በዘመኗ እሱን የመሰለ ድንቅ ተከላካይ አላፈራችም። ፓውሎ ማልዲኒ ፣ አሌሳንድሮ ኮስታ ኩርታ ፣ ማውሮ ታሶቲ ፣ ፍሊፖ ጋሊ እና ክርስቲያን ፓኑቺን የመሰሉ ኮከቦች ብታስመለክትም የፍራንኮ ባሬሲ ግን ይለያል። ፒተር ማን የፍራንሲ ቤከንባኦር ሌላኛው መልክ ይለዋል። በጀርመንኛው "ዴር ኬይዘር" ወይም የመከላከል ንጉሠ ነገሥት እንደማለት ነው።
ጣሊያኖች በተለምዶው የመሃል ተከላካይን ጠራጊው (አፅጂው) ይሉታል። ይህን ስም ወስዶ ያውም ጣሊያን ተወልዶ የማይታትር ባይኖርም ባሬሲ ግን ለዚህ ስያሜ ትክክለኛው ሰው ስለመሆኑ ይነገርለታል። በክለብም ሆነ በብሔራ ቡድን እሱን በማሰልጠን የሚታወቁት አሪጎ ሳኪ ለዚህ ምስክር ናቸው።
"ባሬሲ ከኃላ ካለ የትኛውም የመልሶ ማጥቃትና የተሻጋሪ ኳሶች እንቅስቃሴ አያሰጋኝም ነበር። ከተቆጠረብን ደግሞ ከእሱ ይልቅ አብረውት ከሚጣመሩት ጋር ነበር ችግሬ።" ሲሉፍፁምነትን አላብሰውታል።

ከአስገራሚ የአለማችን የመሃል ተከላካይ ጥምረቶች ቀዳሚው የፍራንኮ ባሬሲ እና የፓኦሎ ማልዲኒ ነበር። እነዚህ ኮከቦች በጋራ 196 ጨዋታዎች አድርገው በአስግራሚ ሁኔታ 23 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠረባቸው፡፡
ለዚህም ይመስላል ፓውሎ ማልዲኒ ስለመከላከል ማጣቀሻ ካስፈለገ ባሬሲ እንደምሳሌ መቅረብ አለበት የሚለው። የፋሽኗ ከተማ ኤስ ሚላን ከባሬሲ በላይ ማንንም አላከበረችም። 1999 ላይ ሚላን የክፍለ ዘመኑ ምርጡ ተጫዋች ብላ ሰይማዋለች። በተጫዋችነት ዘመን እሱ ይለብሰው የነበረውን 6 ቁጥር ትጥቅም ቢሆን መቼም እንዳይለበስ ከልክላለች።
እርግጥ ነው ባሬሲም ለኤስ ሚላን ያለሰጠው ነገር የለም። ለ20 ዓመታት ኳስን ሲጫወት ከኤስ ሚላን ውጪ ሌላ ክለብ ፈፅሞ አያውቅም። በወጥ ብቃት አገልግሏል። 15ቱን ዓመታት ደግሞ በአምበልነት ሚላንን ሲመራ 3 የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፣ 6 የጣሊያን ሴሪኤ ፣ 4 የጣሊያን አሸናፊዎች አሸናፊ እና 2 የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ድሎችን በቆይታው አሳክቷል።
በአስተዋይነቱ፣ ክፍተቶችን በማነፍነፍ እና በጫና ውስጥ ከአካላዊ ፍትጊያ ይልቅ መረጋጋትን መምረጡ ልዩ ያደርገዋል። ባሬሲ የግዛት አስከባሪ የመሪነት አምሳያ ይሉታል። ብዙ አሸንፎ የእግር የኳስ አለምን የገለበጠ ሚላንን ያነገሰ አምበል ጭምር ነው።
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሜዳ ላይ የሚጮህው አንዳንዴም እንደ እብድ የሚያደርገው ባሬሲ ማጥቃት አስጀመሮ ቡድኑን እየመራ አሸናፊ ያደረገባቸው አጋጣሚዎች ቀላል አይደሉም፡፡
እሱ በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተከላካዮች አንዱ ብቻ ሳይሆን የታማኝነት እና የጽናት ምልክት ነው። ከኤሲ ሚላን እና ከጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጋር ያሳለፋቸው የማይረሱ ጊዜያትን በማሰብ ብዙዎች የመከላከል ሚናን ወደ ወርቅ ደረጃ ያሳደገ ብለውታል።

ፍራንኮ ባሬሲ ሀገሩ ጣሊያንንም ቢሆን በተሻለ ጠቅሟል። ስፔን ባሰናዳችው 12ኛው ዓለም ዋንጫ ሀገሩ ምዕራብ ጀርመንን በፍፃሜው 3 ለ 1 አሸንፋ ባለድል ስትሆን ባሬሲ የስብስቡ አካል ነበር። ይህ ትውልድ ጣሊያን ለ3ኛ ጊዜ በዓለም አደባባይ እንድትነግስ በማድረግም ታሪክ ሰርቷል።
ባሬሲ ለመጀመሪያ ጊዜ አምበል የሆነበት የ1994ቱ የአሜሪካው ዓለም ዋንጫ ለጣሊያን እጅግ አስቆጪ ነበር።ራሱን ጨምሮ የባሎን ዶር አሸናፊው ሮቤርቶ ባጂዮን የያዘችው ጣሊያን እስከፍፃሜው ብትጓዝም በብራዚል በመለያ ምት ተሸንፋ ዋንጫውን አጥታለች።
ዛሬ ላይ በእግርኳስ ህይወትህ የሚቆጭህ አጋጣሚ የትኛው ነው ተብሎ ባሬሲ ሲጠየቅ ለቅፅበት እንኳን ሳያስብ የ1994ቱ ዓለም ዋንጫ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ 3 ለ 2 በተጠናቀቀው የመለያ ምት የጣሊያን ብ/ቡድን አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ በአምበላቸው ላይ እምነት ጥለው የመጀመሪያውን የመለያ ምት እንዲመታ ዕድል ሰጡት።
ፍራንኮ ባሬሲ ከዚህች የመለያ ምት አስቀድሞ ለሀገሩና ለክለቡ 24 ጊዜ ፍፁም ቅጣት ምቶችን አግኝቶ 15ቱን ወደ ግብነት ቀይሯቸዋል። 25ኛዋ የመለያ ምት ግን ባሬሲን ከዳችውና ግብ ሳትሆን ቀረች። ከዛማ ዳንኤል ማሳሮና ሮቤርቶ ባጂዮም የባሬሲን ፈለግ ተከትለው መለያ ምቱን ሳይጠቀሙበት ቀሩ።
በወቅቱ ካልቾ ከተሰኘ ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ"ሀገሬ ልትሞሸር ደቂቃዎች ሲቀሯት ደስታዋ ወደ ሀዘን የተቀየረው በእኔ ምክንያት ነው በማለት ራሱን እንደ ጥፋተኛ በመቁጠር ለሀገሩ ያለውን ክብር አሳይቷል፡፡
በ1980 እና በ1988ቱ የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም በ1984ቱ የአሜሪካው ኦሎምፒክ ባሬሲ ከሀገሩ ጋር እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ በመጓዝ ደማቅ ታሪክ ሰርቷል።
ሀገሩ ጣሊያንም ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦና ጉልህ አበርክቶ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኗ በኩል እውቅና ሰጥታዋለች።
ከማርኮ ቫን ባስተን በመቀጠል በ1989ኙ ባሎን ዶር 2ኛ የወጣው ፍራንኮ ባሬሲ በግሉም ቢሆን ቁጥር ስፍር የሌለውን ሽልማቶች አሳክቷል። ከሁሉ በላይ 1989/90 ላይ ዩቬንቱስ የጣሊያን ዋንጫን ሲያሸንፍ ባሬሲ በ4 ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀበት አጋጣሚ ያልተጠበቀውና ለየት ያለው ሽልማቱ ነበር።
ፍራንኮ ባሬሲ ጁሴፔ የተሰኘ ታላቅ ወንድም አለው።ልክ እንደፍራንኮ ሁሉ ታማኝ የኢንተር ሚላን ተጫዋች ነበር። 2 ዓመት ቀድሞ ኳስ የጀመረው ጁሴፔ 1986 ላይ የኢንተር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዘርፍን አሸንፏል። ወንድማማቾቹ ለሁለቱ የሚላን ከተማ ተቀናቃኝ ክቦች አምበል ሆነውም አገልግለዋል፡፡
በአብርሀም ተስፋዬ