Search

በአማራ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሠራሮች ይቀጥላሉ - አቶ ዓለምአንተ አግደው

ሓሙስ ጥቅምት 27, 2018 42

በአማራ ክልል ሰብዓዊ መብትን ማዕከል ያደረገ ውጤታማ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሠራሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የ5 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ትውውቅ እና የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ሰብሳቢ አቶ ዓለምአንተ አግደው፤ ፍትሕን ለማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የፍትሕ እና የዳኝነት አካላት በቅንጅት እና በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በክልሉ የፍትሕ እና የዳኝነት አካላት የትብብር መድረክ ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፍ/ቤት፣ ፍትሕ፣ ፖሊስ እና ማረሚያ ቤትን የያዘው የትብብር መድረክ ተግባር የተሳሰረ በመሆኑ የአንዱ ተቋም ውጤት ለአንዱ ተቋም ግብዓት መሆኑንም ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም በክልሉ በፍትሕ እና በዳኝነት ዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።
የፍትሕና የዳኝነት ዘርፉ በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የዕቅዱ አካል የሆነው የ5 ዓመት መርሐ ግብር ተነድፎ በትውውቅ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ