ኬንያ በዛሬው ዕለት የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ያግዛታል የተባለለትን የግዙፍ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ አስጀምራለች።
በ800 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በናኩሩ ግዛት የከናወነውን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በስፍራው በመገኘት አስጀምረዋል።
ፕሮጀክቱ በቻይናው ካይሻን ግሩፕ እና በኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ኩባንያ በጋራ እንደሚከወን ተገልጿል።

በዓመት 4.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያመርት የተነገረለት ፋብሪካው ተገማች ያልሆነው የማዳበሪያ ዋጋ መዋዠቅ በሀገሪቱ አርሶአደሮች ላይ እያሳረፈው ያለውን ጫና ያቀልላል ብለዋል ፕሬዚዳንት ሩቶ።
አክለውም፥ ይህ ችግር የምግብ ዋጋ መናር፣ የምርት መቀነስ እና የቤተሰብ ገቢ ማሽቆልቆልን አስከትሏል ነው ያሉት።
ኬንያ እአአ በ2023 600 ሺህ ቶን፤ እኤአ በ2025 የመጀመሪያ 6 ወራት ብቻ ደግሞ 443 ሺህ ቶን ማዳበሪያ ከውጭ ማስገባቷን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ የመርከብ ጭነት ለግምጃ ቤታችን ከፍተኛ ወጪ፤ ለሕዝባችን ደግሞ የባከነ ዕድል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የከርሰምድር እንፋሎት ኃይልን በመጠቀም አረንጓዴ አሞኒያን ወደ አፈር ማዳበሪያነት የሚቀይረው ፋብሪካ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በግንባታው ወቅት ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥረው ፋብሪካ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባም ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ኩባንያ በየዓመቱ የ13 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ የሚያስገኝ አዋጭ ፕሮጀክት ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያም በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ መጣሏ ይታወቃል።
ሀገሪቱ በየዓመቱ በአማካይ ከ1.5 ሚሊዮን ቶን በላይ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎችን ከውጭ የምታስገባ ሲሆን፤ አዲሱ ፋብሪካ ግንባታው ሲጠናቀቅ በየዓመዩ በትንሹ የዚህን እጥፍ የሚያመርት ይሆናል።
ይህም ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ይጠበቃል።
በመሐመድ ፊጣሞ