Search

በኦሮሚያ ክልል ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ልማት ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው -የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

ሓሙስ ጥቅምት 27, 2018 32

በኦሮሚያ ክልል ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለልማት ሥራዎች መጠናከር ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ድባብ እና ልማት እንዲኖር፣ ስጋቶች ሲያጋጥሙ ለክልሉ መንግስት አስፈላጊ ጥቆማ እና መረጃ በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድምበሩ እንደገለጹት፤ ሰላምን ማጽናት ትልቁ ኃላፊነት የመንግስት ቢሆንም፣ የፖለቲካ ተዋናዮችም ድርሻ አላቸው።
የጋራ ምክር ቤቱ በተለይም የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ቅድሚያ ትኩረት የሚፈልጉ እንዲሁም መሻሻል በታየባቸው ደግሞ ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ አንጻር ከመንግስት ጋር እየሰሩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
በተለይም በክልሉ ምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ አርሲ እንዲሁም የተወሰኑ የወለጋ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባላቸው መዋቅር ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም የሰላም ችግር መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች እንዲወገዱ ከማድረግ አንጻር ለመንግሥት አስፈላጊ ጥቆማዎችን በመስጠት በርካታ ችግሮች እንዲፈቱ መደረጉንም አክለዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በየቀበሌው ያለውን ሁኔታ በመከታተል ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሰላም ጋር በተያያዘ ለውይይት የሚቀርቡ ጉዳዮች ካሉም፣ ሀሳቦቹን በመለየት ወደ ምክር ቤቱ በማምጣት ውይይት ተደርጎበት ለመፍትሄው በጋራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ችግሮች ሲያጋጥሙም ለመንግሥት አካላት በግልጽ በማቅረብ የሰላም እና የጸጥታ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥትም ከምክር ቤቱ የሚሰጡትን አስተያየቶችን ተቀብሎ እየተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምከር ቤት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘ ምክር ቤት ነው።