ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 30ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) ቅድመ ጉባዔ የሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በብራዚል ቤሌም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መካሄድ ይጀምራል።
እአአ ከኅዳር 10 እስከ 21 በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔም ኢትዮጵያ ተሳትፎ የምታደርግ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት እየወሰደቻቸው ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን አጉልታ የምታሳይበት ይሆናል፡፡
ጉባዔው የዓለም ሙቀት መጨመርን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመገደብ በሚደረገው ጥረት ላይ ያተኩራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ለመወያየት የሀገራት መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እንዲሁም ተደራዳሪዎችን እና የተለያዩ ተዋንያንን ያሰባስባል።
ጉባዔው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙኀን በሺዎች የሚቆጠሩ ተወካዮች የሚሳተፉበት ነው።
በሀብታሙ ተክለስላሴ