Search

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚመልሰው የባሕር በር

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 25

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እያደገ የመጣውን የሀገሪቷን ሕዝብ፣ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚመልስ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ የራስዋ የባሕር በር የነበራት ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ ከፍ ያለ የባሕር ላይ ስልጣኔ የነበራት ሀገርም እንደነበረች አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሀገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ እንዲሁም ከፍ ያለ የደህንነት ስጋትን ከግምት ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የባሕር በር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፡፡
ጋዜጠኛ እና የታሪክ ተመራማሪ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤ ከቀይ ባሕር እና ዓባይ ወንዝ ጋር ተያይዞ ስሟ የሚነሳው ኢትዮጵያ ህልውናዋ ከሁለቱ ውኃዎች ጋር አብሮ የተገመደ ነው ብለዋል፡፡
ለብዙ ዘመናት ትልልቅ መርከቦች የነበራት ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን አቋርጣ ከሌላው ዓለም ጋር የንግድ ልውውጥ ታካሂድ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ ያሉት የታሪክ ተመራማሪው፤ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ሕልውናዋ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቀይ ባሕር እና ዓባይ ለኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸውን ትውልዱ ሊገነዘብ ይገባል ያሉት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፍልስፍና ምሁር ሰለሞን አሊ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ