Search

በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር ይገባል - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 15, 2018 32

11ኛው ጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ሲሆን መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ልዩ መልዕክተኞች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።   

በፎረሙ ላይ አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በሰላምና ደህንነት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የሚገጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (/) በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ሀገራት በራስ አቅም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይገባል።

ወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ መበልጸግ አቀጣጣይ ሞተር እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ትኩረት ይፈልጋሉ ብለዋል።

ከኢንቨስትመንት አኳያም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በአፍሪካ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎች እና ቢዝነስ ተቋማት ኢንቨስት አድረገው አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፋጠን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ትኩረት ይሻል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስት በማድረግ የሥራ ዕድል በመፍጠር ቀጣናዊ ትስስር እንዲጠናከር አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኬኒያ ቴሌኮም ኦፕሬተሮችም በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ናይጄሪያዊው ባለኃብት አሊኮ ዳንጎቴም በኢትዮጵያ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ መሰል የኢኮኖሚ ትስስሮች ለአፍሪካ ብልጽግናና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

የቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ጆአኪም ቺሳኖ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ግንኙነት ቢኖሩም በበቂ ደረጃ ተሳስረዋል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።

ግንኙነቱ መተማመን ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ መተማመንን ማጽናት ወሳኝ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።  

የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆይሴ ባንዳ (/) አፍሪካ መበልጸግ የሚያስችል የተፈጥሮ ጸጋ ቢኖራትም ኃብቱን አልምቶ መጠቀም ላይ ግን ውስንነቶችን መኖራቸውን ገልጸዋል።

ያሉ ዕድሎችን በመጠቀም ለተተኪው ትውልድ ሥራ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሴቶችን ማሳተፍም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #TanaForum