በኢትዮጵያ እና በብራዚል መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ወደ ላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት ደረጃ የሚሸጋገርበት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ተከፍቷል።
የብራዚል የንግድና የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ኤጀንሲ (Apex Brazil) በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ ቋሚ ጽሕፈት ቤቱን ሊከፍት መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ይህንን አጋጣሚ በማስመልከት በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የጽሕፈት ቤቱ መቋቋም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ወደ ተጨባጭ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የኢንዱስትሪ ዕድሎች የሚቀይር ስትራቴጂያዊ ድልድይ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በብሪክስ (BRICS) ማዕቀፍ ውስጥ ያላቸው አባልነት የሁለትዮሽ ንግድን፣ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን እና የጋራ ኢንዱስትሪያዊ እድገትን ለማፋጠን ተጨማሪ ዕድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከአፔክስ ብራዚል ጋር በቅርበት በመስራት በተለይም በአግሪ ቢዝነስና አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኢንዱስትሪ ማምረቻ፣ በአረንጓዴ ኢነርጂ፣ በሎጂስቲክስ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ላይ ትብብሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሙሉ ዝግጅት አድርጓል።
ኮሚሽኑ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ የብራዚል ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ከጅምሩ እስከ ስኬቱ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገባ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም ከኤጀንሲው ፕሬዚዳንት ላውደሚር አንድሬ ሙለር ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የገበያ መረጃ ልውውጥን እና የንግድ ትስስርን የሚያጠናክር ቋሚ መድረክ በመፍጠር የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና የብሪክስ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግር ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: