Search

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ረቡዕ ነሐሴ 27, 2018 113

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤፣ ከዓመታት በፊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የህዝብ ቅሬታ ከሚስተዋልባቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ ነበር ብለዋል።

አሁን ግን ታሪክ መቀየሩን እና በዓመት የማይስተናገድ ዜጋ ጉዳዩን በቀን ውስጥ ፈፅሞ የሚመለስበት ተቋም መሆኑን ገልፀው፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሠራሩን በዲጂታል በማዘመን አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዛሬ በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው እንደተመለከቱት፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቋማዊ ሪፎርምና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎች የተቋሙን ስምና የሥራ ባህል በአዲስ መልክ እየቀየሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማሸጋገሩ ተገልጋዮች ፈጣን፣ ግልጽና እንግልትን የቀነሰ አገልግሎት እንዲያገኙና እርካታቸውም እንዲጨምር እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

አገልግሎቱ በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሱን በማደራጀት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት፣ የቪዛ፣ የጉዞ ሰነዶች፣ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲሁም የአየርና የመሬት ድንበር ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት እያከናወነ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

እያንዳንዱ ሪፎርም የሚለካው ዜጎች በሚያገኙት የአገልግሎት ጥራት፣ በሚቆጥቡት ጊዜና በሚያገኙት እርካታ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተቋማዊ ለውጥም መንግሥት ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ዜጋ-ተኮር የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

በቀጣይም የተቋሙን የዲጂታል ሽግግር በማፋጠን፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ጥራትን በማሳደግ፣ ተቋማዊ ዐቅሙን በማጠናከር እና የተገልጋዮችን እርካታ በተጨባጭ በማረጋገጥ ላይ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

የተገልጋዮችን ሐሳብና ቅሬታ ራስን ለማሻሻል መነሻ አድርጎ መቁጠር ከተቻለ ከዚህም በላይ መለወጥ እንደሚቻል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: