ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የባህል ተቋማት መሪዎችን፣ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት የሰላም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈውን የዓለም አቀፍ ኔትዎርክስ ፎር ሪሊጂየስ ኤንድ ትራዲሽናል ፒስ ሜከርስ የ2026 ዓመታዊ የአማካሪዎች ስብሰባ (AGM) በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናግዳለች።
በመድረኩ ማስጀመሪያ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መዲና፣ የሰው ልጅ መገኛ እንዲሁም የባህሎችና ሃይማኖቶች ብዝሃነት መኖሪያ በመሆኗ ጉባኤውን በማስተናገዷ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስቴር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን፣ ማህበራዊ ወንድማማችነትን እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዚህም የሃይማኖት እና የባህል ተቋማት ለሰላም ግንባታ፣ ለግጭት አፈታት እና ለማህበራዊ ትስስር የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ እና በህገ-መንግስቱም አስፈላጊው ጥበቃ እንደተደረገላቸው አስረድተዋል።
አክለውም ከሳምንት በፊት 4 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውበት በአዲስ አበባ በውጤታማነት የተጠናቀቀውን ሀገራዊ የምክክር መድረክ አንስተዋል።
ይህ የምክክር መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልፀው፤ ለሂደቱ ስኬታማነት የሃይማኖትና የባህል አባቶች ላደረጉት ቀናኢ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ህብረቱ ሀገር በቀል እና አካታች የሆኑ የሰላም ግንባታ ስራዎችን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ሚኒስትር ደኤታው አድንቀዋል፡፡
አክለውም ይህ ጉባኤ ልምድና መልካም ተሞክሮዎች የሚለወጡበት፣ እንዲሁም ማኅበረሰቦች በሰላምና በሰላማዊ አብሮነት የሚኖሩባቸውን መረቦች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ትልቅ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ 56 ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ዓለም አቀፍ ህብረቱ ለኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለሰላም ላበረከተው አስተዋፅኦ ዓለም አቀፍ እውቅና ሰጥቷል::
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: