Search

የአዝጋሚ ጉዞ ማብቂያ፦ ትውልድ ተሻጋሪው የኢትዮጵያ ታላቅ የማንሠራራት ዘመን

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 132

ዘመናትን በፈጀ አዝጋሚ ጉዞ እና በተረጂነት ማቅ ውስጥ አልፋ ዛሬ ታሪኳን በአዲስ ብዕር እየጻፈች ያለችው ኢትዮጵያ፣ የረጅም ጊዜ የእንቅልፍ ዘመኗን አጠናቅቃ በፈጣን የማንሠራራት ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።

ይህ ዕውን ሊሆን የቻለው የትላንትን ጠባሳ ሽሮ፣ ያለፈውን በጎ ዕሴት አስጠብቆ እና የነገን ብሩህ ተስፋ ሰንቆ በተነሳው የመደመር ዕሳቤ ነው።

የመደመር ፍልስፍና አቅምን፣ ዕውቀትን እና ሀብትን በማስተባበር፣ ኢትዮጵያውያን በቁጭት ለዘመናት ከቆዩበት ኋላቀርነት እና ድህነት በአዝጋሚ ሳይሆን በፍጥነት እንዲላቀቁ አድርጓል።

የመደመር መንግሥት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ሙሉ ለሙሉ የማላቀቅ ግብ አስቀምጦ እየሠራ ይገኛል።

የኢትዮጵያን ጀርባ ያጎበጡ የውጭ ዕዳዎችን ጫና ከመቀነስ ጀምሮ በአንድ ማዕከል እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የገቢ አሰባሰብ አቅምን በማሳደግ ሉዓላዊነትን በኢኮኖሚ ጭምር የማረጋገጥ ጉዞው በከፍተኛ ፍጥነት እውን እየሆነ ነው።

ይህ በመደመር መንግሥት የተጠነሰሰው ትውልድ ተሻጋሪ የማንሠራራት ጉዞ በተግባር የሚታይ እውነት ሆኗል።

መቼ ተጀምረው መቼ እንደሚያልቁ የማይታወቁ የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ባሕሎች ተቀይረው፣ በጊዜ እና በጥራት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አዲስ የሥራ ባህል ተተክቷል።

ማዕድናቷን በላቀ የኃላፊነት ስሜት ማውጣት የጀመረችው እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አድርጋ ማቅረብ የቻለችው ኢትዮጵያ፣ የመፈጸም አቅሟ በእጅጉ ተለውጧል።

በተለይም የጉባ ብስራት በሆኑት ፕሮጀክቶቿ የተስፋን ጮራ ፈንጥቃለች።

ይህ በመደመር መንፈስ የተቃኘው ሀገራዊ የማንሠራራት ይበልጥ ጎልቶ እና ደምቆ የሚታየው ደግሞ በመዲናችን አዲስ አበባ የለውጥ ገጽታ ላይ ነው።

መዲናዋ ትናንት የነበረችበትን የድካም ገጽታ አሽቀንጥራ በመጣል፣ ዛሬ በአፍሪካ መድረክ የምትኮራበትን ስማርት ከተማ ለመገንባት በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘች ነው።

የከተሞች ኮሪደር ልማት እና መታደስ የአዲስ አበባን መልክ ከመቀየርም አልፎ የነዋሪዎቿን የአኗኗር ዘይቤ ለውጦታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤየኢትዮጵያ የማንሠራራት ጊዜዋ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ የኢትዮጵያ የማንሠራራት ማሳያ ነች። የሠራቻቸውን ሥራዎች በብዙ መንገድ ለሌሎች ልምድ እያካፈለች ያለች ከተማ ናትበማለት ከተማዋ የኢትዮጵያ የከፍታ እና የመደመር ጉዞ ማንጸባረቂያ መሆኗን ተናግረዋል።

በዚህ የማንሠራራት ሒደት ውስጥ ሌላው ትልቅ ትኩረት ያገኘው ታሪክን እና ድልን ከፍ አድርጎ ለቱሪዝም መስህብነት እና ለትውልድ ማስተማሪያነት መጠቀም ነው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ የትውልዶች መደመር እና የጀግንነት ማሳያ ሲሆን፣ አዲሱ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎች ልማት መዲናዋን ለውጭው ዓለም የቱሪዝም እና የኮንፈረንስ ማዕከል፣ ለልጆቿ ደግሞ የፍቅር እና የአንድነት መሰብሰቢያ እንድትሆን አድርገዋታል።

ከመደመር ዕሳቤዎች ዋነኛው የሆነውን "ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ማሻገር" የሚለውን መርሕ ከንቲባ አዳነች ሲያብራሩ፣የምንሠራው ሥራ ለዛሬ ብቻ አይደለም ለትውልድ ነው። ለነገ ትውልድ ጭምር የሚሸጋገር እንደኛ ዕዳ እንዳይረከቡ ምንዳ ለማስረከብ በፍጥነት የተለያዩ ፈጠራዎችን አክለን እየሮጥን ነው ያለነውበማለት አስረድተዋል።

የማንሠራራት ጉዞው ረጅም ነው፤ ፈተናዎችም ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን በጥሩ ሐሳብ እና በመደመር መንፈስ የተጀመረው የመቀየር ጉልበት እና ይህ እውነተኛ የማንሠራራት ጉዞ መቼም ወደኋላ አይመለስም።

ከገቢ አሰባሰብ ዕድገት እስከ ዲፕሎማሲ አቅም ግንባታ፣ ከቢዝነስ ሥርዓት ማሻሻያ እስከ ዜጋ ተኮር አገልግሎት ድረስ የተመዘገቡት ስኬቶች፣ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን 2023 . አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የሰነቀው ራዕይ የስኬት ዋዜማ ላይ መድረሱን ያሳያሉ።

ይህ ዘመን የዕዳ ሳይሆን የምንዳ፣ የተረጂነት ሳይሆን የሉዓላዊነት፣ መከፋፈልን ትቶ በመደመር ሀገራዊ አቅም የሚፈጠርበት የኢትዮጵያ ታላቅ የማንሠራራት ዘመን ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: