የአንዲት ሀገር የኢኮኖሚ ሽግግር እና እውነተኛ የማንሠራራት ጉዞ የሚለካው በጠንካራ መዋቅራዊ ፕሮጀክቶች፣ በተቋማዊ ግንባታዎች እና አኃዛዊ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ነው።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የለውጥ ጉዞ ከተለያዩ ማሳያዎች አንጻር ስንመዝነው፣ ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እየተቋቋመች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እና የልማት ሽግግር ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን በግልጽ እንገነዘባለን።
የዚህ አዲስ ሀገራዊ የማንሠራራት ምዕራፍ እውነተኛ ማዕዘን ድንጋይ የተጣለው፣ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የገነቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በይፋ በተመረቀበት ታሪካዊ ዕለት ነው። ያ ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ዜና ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በራሷ ለመወሰን የሚያስችል ግዙፍ አቅም እንዳላት በተግባር ያረጋገጠችበት ነበር።
በተለይም፣ በዚሁ የሕዳሴው ግድብ ምርቃት ዕለት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባ ማማ ላይ ሆነው ይፋ ያደረጓቸው ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት የሚጠይቁት “የጉባ ብስራቶች” የዚህ ዘመን ማንሠራራት ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው።
እነዚህ ስትራቴጂያዊ የልማት ፕሮጀክቶች፦ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን አዲሱን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ የሀገርን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት የሚያረጋግጠውን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ፣ 1.5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን በመላ ሀገራችን መገንባት፣ የነዳጅ ማጣሪያን፣ እንዲሁም የጋዝ ማውጣት ሥራዎችን ያካተቱ የነገዋ ኢትዮጵያ ዋልታዎች ናቸው።
የማንሠራራቱን ነባራዊነት የሚያረጋግጠው ሐቅ፣ እነዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በወረቀት ላይ የተንጠለጠሉ ንድፎች ሆነው አለመቅረታቸው ነው። ዛሬ ላይ የአዲሱ የቢሾፍቱ ሜጋ ኤርፖርት ወደ ተግባር መገባቱ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ በይፋ መጀመሩ፣ ለ1.5 ሚሊዮን ግንባታን እውን የሚያደርግ የቤት ግዢ ብድር የፋይናንስ ስምምነት መፈረሙ ሀገራችን ቃሏን ወደ ተግባር እየቀየረች መሆኗን በተጨባጭ ያሳያል።
ይህ ከጉባ የተጠነሰሰው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር፣ በሌሎች የልማት ዘርፎችም ላይ ከታየው አኃዛዊ እመርታ ጋር ተደምሮ ሲታይ የኢትዮጵያን የማንሠራራት ሥዕል ሙሉ ያደርገዋል።
ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥት ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መነሻ በማድረግ የገለጹት ሐሳብ፣ ይሄንኑ መሬት የረገጠ እውነት ቁልጭ አድርጎ የሚያስረዳ ነው፦
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፣ “ይህ ዓመት የኢትዮጵያ የማንሠራራት ዓመት ነው ብለን ነበር። በሁሉም የሥራዎቻችን መስክ በግምገማ በተጨባጭ ያረጋገጥነው እየመጣ ያለው እመርታ እና ለውጥ፣ ይበል፣ ይቀጥል የሚያስብል ነው” ሲሉ ነው የገለጹት።
ይህ ማብራሪያ በቀጥታ የሚገናኘው ከመንግሥት ይፋዊ ሪፖርቶች እና ነባራዊ ክንውኖች ጋር ነው። መንግሥት በቅርቡ ይፋ ያደረገው የ9.2 በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የዚህ አጠቃላይ ጥረት ማሳያ ነው።
ዘርፎቹን በዝርዝር ስንመለከት፦ በእርሻው ዘርፍ ሀገራችን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚሊዮን ሔክታር መሬት በማልማት ከውጭ ጥገኝነት እየተላቀቀች መሆኑ፣ እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ባወጣው ሪፖርት በታሪክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ባስገኘው የቡና ኤክስፖርት የተመዘገበው ተጨባጭ ዕድገት፣ አሁን ወደ ሥራ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ጋር ሲቀናጅ የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት በዘላቂነት ያትማል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተዘጉ ፋብሪካዎች ዳግም ወደ ሥራ መግባታቸው እና በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠሩ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ፣ ከሕዳሴው ግድብ ከሚገኘው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ውጭ ሊታሰብ አይችልም።
በማዕድን ዘርፍም የሕገ-ወጥ ዝውውር ቁጥጥርን ተከትሎ ከወርቅ ምርት የሚገኘው ገቢ የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እያገዘ ይገኛል።
በተጨማሪም፣ ዘመናዊ የተቋም ግንባታ የማንሠራራት ዐቢይ አካል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሡት የ'መሶብ' አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ከ170 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የዜጎችን እንግልት እና ብልሹ አሠራርን የሚያስቀር ዘመናዊ ሥርዓት ነው። የ'ፋልት' የመሠረተ-ልማት አውታር እና እንደ ቴሌብር ያሉ የሞባይል ባንኪንግ ዕድገቶች፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን በማዘመን አዲሱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ በተግባር እየደገፉት ይገኛሉ።
ይህንን ሀገራዊ ዐውድ በጥልቀት ስንመዝን፣ የኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞ በመረጃ፣ በተቋማዊ ግንባታ እና በተግባር የተደገፈ ነባራዊ እውነታ መሆኑን እንረዳለን።
እርግጥ ነው፤ አሁንም ቢሆን የዜጎችን የኑሮ ውድነት ማቃለል እና ዘላቂ ሰላምን በሁሉም አካባቢዎች ማስፈን ጠንካራ ትኩረት የሚሹ ሀገራዊ የቤት ሥራዎቻችን መሆናቸውን አንዘነጋም። ነገር ግን፣ ከሕዳሴው ግድብ ማማ የተቀዳው፣ በሰባቱ የጉባ ብስራቶች የታነጸው እና ዛሬ በተለያዩ ዘርፎች በተጨባጭ ፍሬ ማፍራት የጀመረው ይህ ተሰናስሎ እና ተደምሮ የመጣ የልማት ጅማሮ፣ ሀገራችንን ፈተናዎቿን ተቋቁማ ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ እንድትሻገር የሚያደርግ ጠንካራ ብሔራዊ አቅም ፈጥሯል።
አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ይህንን ነባራዊ የለውጥ ጉዞ በተባበረ ክንድ ከዳር ማድረስ ነው!
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: