Search

የኢትዮጵያ ሴት ወታደሮች እውነተኛ ጀግንነት በጳጉሜን 3 የጽናት ቀን ሲቃኝ

ማክሰኞ ጳጉሜን 03, 2018 66

ሀገር በሴት ትመሰላለችእናት ሀገርየምንላት ኢትዮጵያም የጽናቷ፣ የነጻነቷ እና የማንነቷ ምስጢር ከጀግኖች ሴት ልጆቿ ደምና አጥንት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።

የኢትዮጵያ ሴት ወታደሮች የታሪክ ውርስ ተቀባዮች እና የዛሬይቱ ሀገር ዘብ ሲሆኑ፣ በታሪክም  እቴጌ ጣይቱ ብጡል በዓድዋ ተራሮች ላይ ያሳዩትን ስትራቴጂካዊ መሪነት እና የወንድሞቻቸውን ወኔ ያነሳሳ የውጊያ መስመር ተከተለው ዛሬም በዘመናዊው የመከላከያ ሠራዊታችን ውስጥ ሀገርን በክብርና በጀግንነት በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።

ዛሬ ጳጉሜን 3 ቀን የሚከበረው የጽናት ቀን፣ እነዚህን የእውነተኛ ጽናትና የሀገር ፍቅር ምሳሌዎች የሆኑ የኢትዮጵያ ሴት ወታደሮችን በከፍተኛ ኩራት እና አክብሮት የምናስታውስበት ልዩ ዕለት ነው።

እነዚህ ጀግኖች የሀገርን ዳር ድንበር እና የሉዓላዊነት ድንበር በጽናት ከመጠበቅ ባሻገር፣ ከሀገር ውስጥ አስቸጋሪና ፈታኝ ግዳጆች እስከ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ድረስ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በከፍተኛ ብቃትና በላቀ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ተወጥተዋል።

በበረሃው እሳት፣ በሸለቆው ቁር፣ በውጊያው የፊት መስመር እና በፍልሚያው ማዕበል ውስጥ ሳይበገሩ ሀገራዊ ጥሪን በመቀበል ያሳዩት ቁርጠኝነት የጽናታቸውን ጥግ ያመላክታል። በጦር ሜዳ ላይ የሚያሳዩት አይበገሬነት፣ በመድፍና በጥይት ድምፅ መካከል የሚያሳዩት የረጋ ጀግንነት የሀገርን ዋስትና ያጠናከረና ለትውልድ የሚሻገር ትልቅ የጽናት ትምህርት ነው።

የኢትዮጵያ ሴት ወታደሮች የጀግንነትና የሰብዓዊነት ተልዕኮ በሀገር ድንበር ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር በሶማሊያ፣ በሱዳን (አብዬ) እና በሌሎች የዓለም ግጭት ቀጣናዎች ተሰማርተው ያሳዩት ከፍተኛ የሙያ ብቃት፣ የደፋርነት መንፈስ እና ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው የጠበቀ ወታደራዊና ሰብዓዊ ግንኙነት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ድንቅ አድናቆት አትርፎላቸዋል።

ሰላምን በማስከበር፣ ጥቃት የደረሰባቸውን እናቶችንና ሕፃናትን በመጠበቅ ረገድ ያሳዩት ልዩ ጥበብና ግርማ ሞገስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለጽናታቸው፣ ለተጋድሏቸው እና ለሰላም ላበረከቱት አስተዋጽዖ ልዩ የሜዳሊያና የክብር ዕውቅና እንዲሰጣቸው አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሴት ወታደሮች የመከላከያ ኃይላችን የጀርባ አጥንት፣ የሰላማችን መሠረት እና የሀገራችን የጽናትና የኩራት ሕያው ምልክቶች ናቸው። በሴትነታቸው እናትነትንና ርኅራኄን፣ በወታደርነታቸው ደግሞ ወኔንና አይበገሬነትን አዋህደው በመያዝ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያውለበልባሉ።

በዛሬው ጽናት ቀን፣ የሀገርን ክብርና ነጻነት ለማስከበር በየግንባሩ ለከፈሉት እና አሁንም በመስዋዕትነት ላይ ለሚገኙት የጽናት ጥግ የሆኑ ጀግኖች ሴት ወታደሮቻችን ታላቅ አክብሮት፣ ውዳሴና ምስጋና ይገባቸዋል።

 

በኃብተሚካኤል ክፍሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: