ኢትዮጵያ የግብርና ሀገር ናት፤ ግብርና ለሀገራችን ኢኮኖሚ፣ ለዜጎች ኑሮና ለምግብ ዋስትና ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በተለምዶ የሀገራችን ግብርና በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ለድርቅና ለተለዋዋጭ አየር ሁኔታ ተጋላጭ ነበር። ይህም በምርት መጠን፣ በአርሶ አደሩ ገቢና በምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድር ነበር።
በአንፃሩ አሁን ላይ የሀገራችን ግብርና ወደ አዲስ የሽግግር ምዕራፍ እየገባ ነው። የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የማምረት አቅምን በማሳደግ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ ዓመቱን ሙሉ ወደ ማምረት እየተሸጋገረ ይገኛል። ይህም የዘርፉን ማንሠራራት እውን ያደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው።
የዚህ ሽግግር ዋና መሠረት የመስኖ ልማት ነው። የውሃ ሀብታችንን በአግባቡ በመጠቀም ከዝናብ ወቅት ውጪም ምርት ማምረት ችለናል። በተጨማሪም የመስኖ ልማቱ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ለማምረት ዕድል በመፍጠር የምግብ አቅርቦትንና የአምራቹን ገቢ ለማሳደግ አስችሏል።
የግብርናው ሽግግር የምርት መጠንን ብቻ የሚመለከት አይደለም፤ የምርቱ ዓላማም እየተለወጠ ነው። በዋናነት ለቤተሰብ ፍጆታ ይውል የነበረው ምርት የገበያ ፍላጎትን ያገናዘበና ገቢ የሚያመነጭ እየሆነ መጥቷል። ጥራትን ማሻሻል፣ ምርትን በዕቅድ ማምረትና ለገበያ ማቅረብ የዚህ ለውጥ ዋና መገለጫዎች ናቸው።
የተሻሻሉ ዘሮች፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችና የተሻሻሉ የእርሻ ዘዴዎችም ምርታማነትንና የምርት ጥራትን ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው። ከዚህ ጋር የምርት ማከማቻ፣ ማጓጓዣ፣ ማቀነባበሪያና ገበያ በተገቢው መንገድ መተሳሰራቸው እሴት በመጨመር ምርትን ለማሸጋገር ያስችላል። ይህም ለአምራቹ የተሻለ ገቢና ለሀገራችን ኢኮኖሚም ተጨማሪ ጥቅም ያስገኛል።
የግብርና ማንሠራራት ከዝናብ ጥገኝነት ወደ መስኖ ልማት፣ ወቅትን ጠብቆ ከማምረት ዓመቱን ሙሉ ወደማምረት፣ ለራስ ፍጆታ ከማምረት ወደ ገበያ-ተኮር አምራችነት የሚደረግ ሰፊ ሽግግር ነው።
ይህ ለውጥ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግና የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ለሀገራችን ማንሠራራት ጠንካራ መሠረት እየጣለ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: