በማንሠራራት ቀን የሀገራችንን የልማት ምዕራፍ ስናበስር፣ የኢትዮጵያ ቀጣዩ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ የሆነው የኮይሻ የውሃ ኃይል ፕሮጀክት አጠቃላይ ግንባታ አፈጻጸም ሀገራዊ ተስፋን በፈጠረበት ዓመት ነው።
201 ሜትር ቁመት ያለው ይህ ግዙፍ ግድብ 6.4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአፈር ቁፋሮ ማካሄድ የተቻለበት ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ አዲስ ከፍታ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
የግንባታው አፈጻጸም በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ግድቡ ከሚፈልገው 7.72 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ውስጥ 81.2 በመቶው ማለትም 6.27 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል።
የኃይል ማመንጫ ቤቱ የቁፋሮ ሥራ እንዲሁም የሲቪል ሥራው የመጀመሪያ ደረጃ የኮንክሪት ሙሌት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሙሉ ፕሮጀክቱን በታቀደው ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት የሌት ተቀን ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የ1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የኃይል ማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጎን ለጎን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የማይነቃነቅ የኃይል ማዕከል የሚያደርጋት ቀጣዩ ታላቅ የልማት ማሳያ ነው።
ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎትን ከማሟላቱም በላይ የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት አቅማችንን በማሳደግ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ማንሠራራት በጽኑ መሠረት ላይ የሚተክል ይሆናል።
በንብረቴ ተሆነ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: