Search

በቴክኖሎጂ የተሳለጠው የኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞ

ሰኞ ጳጉሜን 02, 2018 128

ዓለም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ፋይናንስ እና በፈጣን የመረጃ ፍሰት እየተመራች በምትገኝበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂው ዘርፍ አዲስ ሀገራዊ የፈጠራ እና የማንሠራራት ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።

ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሀገራችንን ከባህላዊ የአሠራር ዘይቤ በማውጣት ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ኢኮኖሚ እያሸጋገሯት ይገኛሉ።

ይህ የቴክኖሎጂ ማንሠራራት መነሻውን ያደረገው የመሠረተ ልማት ግንባታን በማስፋፋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ላይ ነው።

በተለይም የቴሌኮም ዘርፉ መስፋፋት፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በየደረጃው መተግበሩ እና የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አሠራር መሸጋገራቸው የዜጎችን የዕለት ተለት ሕይወት ከመቀየር ባለፈ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በከፍተኛ ደረጃ አፋጥኖታል።

በተጨማሪም የሰው ኃይል እና የወጣቶች የፈጠራ አቅም ልማት የዚህ ማንሠራራት ዋንኛ  አካላት ናቸው።

“5 ሚሊዮን ኮደሮች በመሳሰሉ ሀገራዊ መርሐ-ግብሮች አማካይነት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በሶፍትዌር ማበልጸግ፣ በዳታ አናሊቲክስ እና በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የላቀ እውቀት እየጨበጡ ይገኛሉ።

ይህም ወጣቶች በሀገር ውስጥ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ስታርታፖችን እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት ኤክስፖርት አቅም እንዲገነባ መንገድ ከፍቷል።

በዚህ የዲጂታል ዘመን ኢትዮጵያ እያሳየችው ያለው የቴክኖሎጂ እመርታ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ግልጽነትን ለማስፈን እና ሀገራችንን በምስራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረ የፈጠራ እና የማንሠራራት የማይገታ ጉዞ ነው።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: