Search

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ

ማክሰኞ ጳጉሜን 03, 2018 18

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለግድቡ መጠናቀቅ የገንዘብ፣ የጉልበት እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (/) እንደተናገሩት፣ የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያንን የማይበገር ታላቅ የጽናት ተምሳሌትነት ለዓለም ያሳየና በኅብረት ከተነሳን የማናሳካው ዓላማ እንደሌለ በተግባር ያረጋገጥንበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከእርዳታና ከጥገኝነት ለመላቀቅ ባሳዩት ቁርጠኝነት ያደረጉት ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ግድቡ ያለ ምንም የውጭ ብድርና እርዳታ በራስ አቅም ብቻ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

ባለፉት 14 ዓመታት የሕዝብና የመንግሥት የተቀናጀ ርብርብና ጽናት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ግድቡ ለፍጻሜ እንዲደርስ ማስቻሉን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም አቅማችን የሀገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ከፍታ በማጎልበት ለሌሎች ሀገራዊ የልማት ስራዎች ታላቅ ብርታት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (/) ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የሀገራችን ወዳጆች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አያይዘውም በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት የተመዘገበውን የጋራ የርብርብ፣ የአንድነትና የመደጋገፍ መንፈስ በጽናት በማጠናከር የኢትዮጵያን የልማትና የሰላም ጉዞ ወደ ላቀ የከፍታ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል።

 

በወንድማገኝ ሃይሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: