Search

የመስከረም ሽታ፦ የትናንት ትዝታችን፣ የነገ ተስፋችን

ዓርብ መስከረም 01, 2019 59

አንዳንድ ወራት በቀን መቁጠሪያ ላይ ከሰፈረ ስም በላይ ጥልቅ ትርጉም አላቸው፤ መስከረም ደግሞ ከእነዚህ ሁሉ የላቀ ነው።

የክረምቱ ጭጋግ ተገፍፎ፣ ሰማዩ ጠርቶ፣ ምድር በአደይ አበባ እና በአረንጓዴ ለምለም ስታሸበርቅ፣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ አዲስ ተስፋ እና የልጅነት ትዝታ አብሮ ይፈካል።

አዕምሯችንን ወደ ኋላ ስንመልስ፤ በትምህርት ቤት ሜዳ በሣር ተጠላልፈን የወደቅንባቸው የሳቅ ቅጽበቶች፣ የልጃገረዶች "አበባ አየሽ ሆይ" ዝማሬ፣ የሌሊቱ የዶሮ ወጥ እና የጠዋቱ የቡና መዓዛ ዛሬም ሕያው ሆነው ይሰሙናል።

እነዚህ የጋራ ትዝታዎቻችን ከጂኦግራፊ እና ከቋንቋ ልዩነቶች በላይ ልባችንን የሚያስተሣሥሩ ጥብቅ ክሮች ናቸው።

"እንቁጣጣሽ" የሚለው ቃል ራሱ ጥልቅ ታሪካዊ ውበት አለው። ኖኅ ምድሪቱን በአደይ አጊጣ ሲያያት "ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ" እንዳላት፣ ወይም ንግሥት ሳባ ከንጉሥ ሶሎሞን "ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ" ተብላ ቀለበት እንደተበረከተላት ይነገራል። ከዚህም ባለፈ፣ መስከረም እኛን ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርጉን ታላላቅ ታሪኮቻችንን እንድናስብ ያደርገናል።

የዓድዋ ዐርበኞች ከየአቅጣጫው ተሰባስበው፣ በልዩነታቸው ሳይከፋፈሉ በአንድነት ቆመው የሀገርን ክብር እንዳስጠበቁ ሁሉ፣ መስከረምም የዚያን ሕያው የአንድነት መንፈስ ነጸብራቅ ይዞ ብቅ ይላል።

በየቤቱ የሚፈላው ቡና እና በየአደባባዩ የሚሰማው ዜማ፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን በጋራ የምንቆምባት አንዲት ጽኑ ሀገር እንዳለችን የሚያረጋግጡልን ሕያው ትርክቶቻችን ናቸው።

ዓመታት ነጉደው ከተሞች ቢለወጡም፣ የመስከረም ሽታ ዛሬም ያው ነው። በአዲሱ ዓመት አዲስ ልብስ እንደምንለብስ ሁሉ፣ ልባችንንም በአዲስ ተስፋ እናድሳለን።

እንደ ዕንቁ የከበረች ሀገራችንን ለመጠበቅ፤ ካለፈው የታሪክ ቁርሾ ወጥተን፣ ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር የጋራ ምክክር፣ በይቅርታ እና በፍቅር አብረን እንጓዝ።

መስከረም እውነተኛውን የሰላም ዕንቁ የምናገኝበት፣ የጋራ ታሪካችንን የምናጎለብትበት ብሩህ ዘመን ይሁንልን!

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: