Search

አደይ አበባ፦ የዘመን መለወጫ የተፈጥሮ ፊርማ

ዓርብ መስከረም 01, 2019 57

የክረምት ጭጋግ ገፈፍ ብሎ፣ ሰማዩ ንፁህ ሰማያዊ ቀለም ሲላበስ፣ የተፈጥሮ ዑደት አንድ ምዕራፍ ዘግቶ አዲስ ሊጀምር መሆኑን ይነግረናል።

ጋራ ሸንተረሩ አረንጓዴ ምንጣፍ ሲለብስ፣ የዚህ ሁሉ ውበት ዘውድ ሆና ብቅ የምትለው ደግሞ አደይ አበባ ናት።

ክረምቱ አልፎ ብሩሁ የፀደይ ወቅት መግባቱን የምናውቀው የቀን መቁጠሪያን በማየት ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጥሮ በራሷ ጊዜ በምትሰጠን በዚህ ቢጫ ገጸ በረከት ነው።

የአደይ አበባ ፍካት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጥልቅ ትርጉም አለው። የመጀመሪያዋ አደይ ስትፈካ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከጭጋግ ወደ ተስፋ የመሻገራችን ማሳያ ናት።

መስከረም ሲጠባ አዲስ ዓመት ይዞት የሚመጣውን አዲስ ራዕይ፣ ይቅርታ እና ተስፋ በማብሰር፣ ሰዎች የየራሳቸውን የዘመን ትዝታ እያወሱ ወደ መስኩ ጎራ እንዲሉ ታደርጋለች።

ለመሆኑ መስከረም ሲጠባ፣ በተለይም በተራሮች እና በኮረብታማ ሥፍራዎች ላይ አሸብርቃ የምትታየው አደይ አበባ ምንድን ናት?

እናት አበባ እየተባለች የምትጠራው አደይ አበባ፣ በዕፅዋት ሳይንስ አጠራር ባይደንስ ማክሮፕቴራ ዝርያ ስር የምትመደብ ውብ እና ሀገር በቀል ተክል ናት።

አፍሪካ ውስጥ ወደ 64 የሚጠጉ የተለያዩ የአደይ አበባ ዝርያዎች እንዳሉ ይነገራል፤ ከእነዚህም ውስጥ 20 የሚሆኑት ልዩ ዝርያዎች መገኛቸው ኢትዮጵያ ነው።

የአደይ አበባ ዑደት እጅግ አስገራሚ ነው። ዘሯ ለዘጠኝ ወራት ያህል በማኅፀነ ምድር ውስጥ ተደብቆ ከቆየ በኋላ፣ በሰኔ እና ሐምሌ ወራት ዝናቡን ተከትሎ መብቀል ይጀምራል። መስከረም ሲጠባ ደግሞ ዐይንን በሚማርክ እና ነፍስን በሚያረካ ጥሩ መዓዛ፣ መስኩን እና ጋራውን በቢጫ ቀለም ታስጊጠዋለች።

በታሪካችን እና በባህላችን ውስጥ አደይ አበባ የዘመን መሻገሪያ እና የደስታ መግለጫ ሆና ኖራለች። ልጃገረዶች "አበባ አየሽ ወይ/ አበባ አየሁሽ" እያሉ ሲዘፍኑ ይህችንው አደይ አበባ እየነቀሉ ለታላላቆች በማበርከት ምርቃት ይቀበላሉ።

ፈረንጆቹ ይህን ተፈጥሯዊ ትሥሥራችንን ሲረዱት፣ አበባዋን Ethiopian Meskel Daisy (የኢትዮጵያ የመስቀል አደይ) የሚል ስያሜ እንደሰጧት ይነገራል። ይህ ስያሜ አበባዋ ከእንቁጣጣሽ ባሻገር፣ በመስቀል በዓል ላይ ከሚለኮሰው ደማቅ የደመራ ችቦ ጋር ያላትን ታሪካዊ ዝምድና ያጎላዋል።

አደይ አበባ ተፈጥሮን ከማስዋብ እና ዘመን ከመለወጥ ባለፈ፣ የጤና እና የፈውስ ምንጭም ናት። በሳይንሳዊ ምርምርም ሆነ በሀገር በቀል እውቀት እንደተረጋገጠው፣ ይህች አበባ ለመድኃኒትነት ትውላለች።

በተለይም በኢትዮጵያ የባህል መድኃኒት ቀማሚዎች ዘንድ፣ የአበባው ቢጫ ክፍል ለተለያዩ ሕክምናዎች ሲውል ኖሯል።

አደይ አበባ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ጌጥ፣ የታሪካችን እና የባህላችን አካል፣ እንዲሁም የፈውስ እና የተስፋ ተምሳሌት ናት።

አበባዋ ፈክታ የምትቆየው ለጥቂት ሳምንታት ቢሆንም፣ በየዓመቱ ይዛልን የምትመጣው መልዕክት ግን ለዘመናት ሲሸጋገር የኖረ፣ ትውልድን ከትውልድ የሚያስተሳስር ደማቅ ዐሻራ ነው።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: