ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓሏን በድምቀት ስታከብር፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ የደስታ መግለጫ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭገኒ ተሬኪን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆን ገልጸው የኢትዮጵያን የባህል ብዝኃነት አድንቀዋል።
አምባሳደሩ “የኢትዮጵያ ወንድሞቼ እና እኅቶቼ በመጪው ዓመት ስኬትን፣ መልካም ዕድልን እና ብልጽግናን እንዲያገኙ እመኛለሁ” ብለዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የቆየ ወዳጅነት እና ጥልቅ ትብብር በአዲሱ ዓመት አዳዲስ ምዕራፎችን እንደሚከፍት እምነታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም የካናዳ ኤምባሲ አዲሱ ዓመት የደስታ፣ የብልጽግና እና የተድላ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የአውስትራሊያ ኤምባሲ ደግሞ መስከረምን “የዳግም መወለድ እና የተስፋ ወቅት” በማለት ገልጾት፤ በአዲሱ ዓመት የፍቅር ትሥሥርን በማጠናከር ለሰላማዊ ዘመን አዲስ ተስፋን መቅረጽ እንደሚገባ አስታውሷል።
የቻይና ኤምባሲ በበኩሉ፣ እንቁጣጣሽን ከወጣቶች ጋር በደማቅ የባህል ትርዒት ማክበሩን ገልጿል። “የኤምባሲያችንን ግቢ በበዓል ድምቀት እና በደስታ ስሜት ስለሞላችሁልን እናመሰግናለን” ሲሉ የቻይና ዲፕሎማቶች ለወጣቶቹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: